ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የቦንድ ሽያጭ ተከናወነ

ሐረር፤ ሚያዚያ 8/2013(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ከቦንድ ሽያጭ መገኘቱን በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የሐረር ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ለግድቡ ግንባታ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ  ተናግረዋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ  እንዳሉት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች እየተዟዟረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ይህንን ምክንያት በማድረግም ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የማሰባሰብና የህብረተሰቡን ግንዛቤን የማስፋት ተግባር ከመከናወኑም በላይ   ባለፉት ሶሰት ወራት ብቻ  ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የቦንድ ሽያጭ መከናወኑን አስታወቀዋል፡፡ 

የግድቡ  ግንባታ ኢትዮጵያን ወደ እድገትና ብልጽግና ጎዳና የሚያሸጋግር  ፕሮጀክት በመሆኑ  ዜጎች በድጋፍ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

 አቶ ሄኖክ  ባለፉት አስር ዓመታት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በክልሉ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል።

ከሐረር ከተማ  ነዋሪዎች መካከል አቶ ፍጹም ብርሃን  ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት፤ ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ እንዲውል ቀደም ሲል የ3 ሺህ ብር ቦንድ   መግዛታቸውን አስታውሰው አሁን ላይም  የ2 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡

ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ህዝቡን በማነሳሳት ለግድቡ ግንባታ  የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ጠቁመው  በቀጣይም የግድቡ  ግንባታ  እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን  አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

የሐረር መናኸሪያ  ጫኝና አውራጅ አገልግሎት ሰጪ ህብረት ስራ ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ አሸናፊ ወንድሙ በበኩላቸው፤ "በማህበሩ ስም የ50 ሺህ ብር ቦንድ ገዝተናል ፤ በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቀ እያደረግን ያለውን  ድጋፍ  እንቀጥላለን " ብለዋል፡፡    

በኢትዮጵያዊያን የመዋጮ ገንዘብ እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ   ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚይዝ ሲሆን በአፍሪካ  ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግዙፍ ግድብ  እንደሚሆን የሚጠበቅ ፕሮጀከት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም