የተዘጋጀልን የሰፈራ መንደር ከመሬት መንሸራተት አደጋ ታድጎናል....የቦሎሶ ሶሬ ወረዳ አርሶ አደሮች

59
ሶዶ ሀምሌ 24/2010 የተመቻቸልን የሰፈራ መንደር ከመሬት መንሸራተት አደጋ ታድጎናል ሲሉ በወላይታ ሶዶ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የቦሎሶ ሶሬ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ። ከወረዳው ከአፋማ ባንጫ ቀበሌ ተነስተው ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ ከተደረጉት መካከል አርሶ አደር ይገዙ ዘለቀ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም የሚኖሩበት አካባቢ ተዳፋታማ በመሆኑ ለመሬት መንሸራተት አደጋ  ሲጋለጡ ቆይተዋል። "በተለይ ክረምት በመጣ ቁጥር ኑሯችን ስጋት ላይ ይወድቅ ነበር “ ያሉት አርሶ አደሩ አሁን በሰፈሩበት ደንጋራ ማዳልቶ ኦቤ ጃጌ መንደር የተሻለ ህይወት እየመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በአዲስ መልክ በሰፈሩበት አካባቢ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋምና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች የተሟሉሏቸው መሆኑን ገልፀዋል። በመሬት ናዳ ምክንያት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸው ስጋት የተሞላበት እንደነበር የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ባሳ ዴሌ ናቸዉ፡፡ አርሶ አደሩ አንዳሉት በመሬት መንሸራተት አደጋ እንስሳትና ሰብል እየወደመባቸው ለጉዳት ተዳርገው ቆይተዋል። “መንግስት ከአካባቢው አንስቶ ወደ ሌላ መንደር እንዲሰፈሩ በማድረጉ ከስጋት ህይወት ተላቀናል “ብለዋል ። የወላይታ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ታውሌ በበኩላቸው በአፋማ ቀበሌ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ በሚደርስ የመሬት መንሸራተት ተጋላጭ የሆኑ 35 አባወራ አርሶ አደሮች ተነስተው ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ መደረጉን ተናግረዋል። አቶ ክፍሌ እንዳሉት ከዞኑ አስተዳደርና ከቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በተገኘ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለአርሶ አደሮቹ በሰፈሩበት መንደር የመኖሪያ ቤትና ሌሎች አገልገሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች እንዲማሉ ተደርጓል። ሌሎች ከ170 በላይ አባወራዎችን ከስጋት አካባቢ በማንሳት ወደምቹ አካባቢ ለማዛወር በአሁኑ ወቅት ነጻ መሬት የማፈላለግና ግብአት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም