ቀጥታ፡

ከአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የሚወጣው መጥፎ ሽታ ለጤና እክል እያጋለጠን ነው - የአካባቢው ነዋሪዎች

ሐምሌ 24/2010 ከአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በሚወጣው መጥፎ ሽታ ለተለያየ የጤና እክል እየተጋለጡ መሆናቸውን የቄራ አካባቢ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ችግሩ የተፈጠረው ወደ አካባቢው የሚወጣውን መጥፎ ሽታ ለመቀነስ የሚጠቀምበት መሳሪያ በመበላሸቱ መሆኑን  አምኗል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አስራት አበራ ለኢዜአ እንዳሉት ከድርጅቱ የሚወጣው መጥፎ ጠረን በስራቸውና ጤንነታቸውም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያደረሰባቸው ነው፡፡ ችግሩ ከጤና በተጨማሪ ማህበራዊ ህይወታቸውንም እያወከው መሆኑን ነው አስተያየት ሰጪው የተናገሩት፡፡ ወተትና የወተት ተዋጽኦዎችን በመሸጥ የሚተዳደረው ወጣት ገላና አወቀ በበኩሉ ከድርጅቱ በሚወጣው መጥፎ ሽታ ምክንያት ደንበኞቹ እየራቁት በመሆኑ ገቢው ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረበት ገልጿል፡፡ ክረምቱን ተከትሎ ከድርጅቱ የሚወጣው መጥፎ ሽታ መባባሱን የገለጸው ወጣት ገላና ቸግሩ በተለይ በህጻናት ጤና ላይ ሊያደርስ የሚችለው የጤና እክል እንዳሳሰበውም ነው የተናገረው፡፡ አቶ ፍጹም ገብረኪዳን የተባሉት አስተያየት ሰጪም ከድርጅቱ በሚወጣው መጥፎ ሽታ ምክንያት እራሳቸውን እንደሚያማቸው ተናግረዋል፡፡ ችግሩ በተለይ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ባሉባቸው ነዋሪዎች ላይ የጎላ ተጽእኖ እያሳደረባቸው መሆኑም ጠቁመዋል፡፡ ችግሩ የቆየ ቢሆንም እስከ አሁን መፍትሔ የሚሰጥ አካል አለመገኘቱንም ነው ያብራሩት አቶ ፍጹም፡፡ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ንብረት በቃ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከድርጅቱ የሚወጣውን መጥፎ ሽታ ለመቀነስ ጥረት ሲደረግ መቆቱን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የስጋ ተረፈ ምርቶች በሚቀቀሉበት ወቅት የሚወጣው ሽታ በአካባቢው ችግር እየፈጠረ መሆኑን አልደበቁም፡፡ ለዚህም ድርጅቱ ከአሁን በፊት  መጥፎ ሽታ ወደ አካባቢው እንዳይወጣ ለመቆጣጠር አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው መሳሪያ በመበላሸቱ ችግሩ መባባሱን  ጠቅሰዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ ቄራ ለመገንባት የ70 ሚሊዮን ብድር ማግኘቱን ገልጸው ችግሩን በፍጥነትና በዘላቂነት ለመፍታት ግንባታውን በፍጥነት ማከናወን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ የህብረተሰቡን ቅሬታ በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ባለስልጣንና በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ “የቀረበልን ቅሬታ ባለመኖሩ ስለችግሩ እውቅና  የለንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም