በ21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚካፈለው የኢትዮጵያ ሉዑክ ሽኝት ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
በ21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚካፈለው የኢትዮጵያ ሉዑክ ሽኝት ተደረገለት
አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 ናይጄሪያ በምታስተናግደው 21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ሽኝት ተደረገለት። በናይጄሪያ አሳባ ከተማ ከነገ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው ውድድር የ20 ኪሎ ሜትር ርምጃን ጨምሮ ከ100 ሜትር እስከ 10 ሺህ ሜትር ርቀት ሩጫ ወድድሮች ኢትዮጵያ ትካፈላለች። በተጨማሪም በዝላይ፣ ውርወራና ጦር ባሉ የሜዳ ላይ ስፖርታዊ ውድድሮች ትካፈላለች። ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታዎች በ64 አትሌቶች የምትወከል ሲሆን 34 ወንዶችና 30 ሴቶች አትሌቶች ይሳተፋሉ። የኢትዮጵያ አትቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በሽኝት ስነ-ሰርዓቱ ላይ ባደረገው ንግግር አትሌቶቹ በውድድሩ ላይ መልካም ስነ-ምግባር በተሞላበት መንገድ እንዲሳተፉ አሳስቧል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክትር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው በ21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘገቡ አትሌቶች ለኦሎምፒክ ውድድር የሚያበቃ ስልጠና እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል። ''በቅርቡ በአልጀርስ ከተማ በተካሄደው ውድድር ላይ ከአገሮች የተማርነው ነገር፤ ለኦሎምፒክ ውድድር ቀደም ብለው አትሌቶችን በመልመል ስልጠና መስጠታቸው ለውጤት ያበቃቸው መሆኑን ነው'' ሲሉ ዶክተር አሸብር ተናግረዋል። ኢትዮጵያም ከ2 ዓመት በኋላ በጃፓን ቶኪዮ ለሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ከወዲሁ ዝግጅት ለመጀመር የኦሎምፒክ ኮሚቴው ማቀዱን ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ጠቁመዋል። በዚህም መሰረት ከ21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናና ሌሎች ውድድሮች ላይ ጥሩ አቅም ያላቸውን አትሌቶች ተመልምለው ወደስልጠና እንደሚገቡ ተናግረዋል። ሁለት የአትሌቶች ተወካች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴሬሽኑና ከኦሎምፒክ ኮሜቴው አመራሮች የተረከቡ ሲሆን በውድድሩ የሚካፈሉ አትሌቶች በቅድመ ዝግጅቱ ጥሩ ልምምድ መስራታቸውን በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል ከሁለት ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ በተዘጋጀቸው 20ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በአንድ ወርቅ፣ ሁለት ብርና ሶስት ነሐስ ሜዳሊያዎች 8ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል።