ኢትዮጵያ በአፍሪካ የቮሊቦል ውድድር በአራት ክለቦች ትወከላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የቮሊቦል ውድድር በአራት ክለቦች ትወከላለች
ሚያዚያ 06/2013 በቱኒዚያ በሚካሄደው የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያ አራት ክለቦችን ታሳትፋለች።
ክለቦቹ ለውድድሩ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየምና በራስ ሃይሉ ጅምናዚየም ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸው ተገልጿል።
የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን (ሲአቪቢ) አዘጋጅነት በቱኒዚያ በወንዶች ለ39ኛ ጊዜ በሴቶች ለ32ኛ ጊዜ ይካሄዳል።
የወንዶቹ ውድድር ከሚያዚያ 8 እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን የሴቶቹ ውድድር ደግሞ ከሚያዚያ 11 እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ይከናወናል።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ኢትዮጵያ በውድድሩ በወንዶች በወላይታ ዲቻና በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ እንደምትወከል ገልጸዋል።
በወንዶች በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ የመጀመሪያ ዙር ምዝገባ አድርጎ የነበረው ሙገር ሲሚንቶ የመጨረሻውን ምዝገባ ባለማድረጉ ምክንያት በውድድሩ ላይ እንደማይሳተፍ ተናግረዋል።
በሴቶቹ ውድድር ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
ወላይታ ዲቻና መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ነገ ወደ ቱኒዚያ የሚያመሩ ሲሆን ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ሰኞ ሚያዚያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ውድድሩ ስፍራ እንደሚያቀኑ ነው አቶ ተክሉ የገለጹት።
አራቱ ክለቦች ለውድድሩ በራስ ሃይሉ ጅምናዚየምና በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
ክለቦቹ በውድድሩ ላይ መሳተፋቸው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ያሉበትን አቋም ለመፈተሽና ልምድ ለማግኘት እንዲሁም ክለቦቹ አገራቸውን በአፍሪካ መድረክ የሚያስተውቁበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
እ.አ.አ በ2020 የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መሰረዙን አስታውሰዋል።
የአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን የዘንድሮውን የክለቦች ውድድር ግብጽ እንድታዘጋጅ መርጧት የነበረ ቢሆንም በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም ውድድሩ የሚካሄድበትን ቦታ ወደ ቱኒዚያ መቀየሩን አስረድተዋል።
ኮንፌዴሬሽኑ የውድድሩን ቦታ የቀየረበትን ምክንያት አለማሳወቁን ነው አቶ ተክሉ ያስረዱት።
ወላይታ ዲቻና ሙገር ሲሚንቶ እ.አ.አ 2019 በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር በመሳተፍ በቅደም ተከተል 18ኛና 19ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቃቸው አይዘነጋም።
የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር እ.አ.አ በ1980 የተጀመረ ሲሆን የግብጹ አል አህሊ 14 ጊዜ፣ የቱኒዚያው ሲኤስ ሰፋክሲያን ስድስት እንዲሁም የግብጹ ዛማሌክ አምስት ጊዜ አሸናፊ ሆነውበታል።
የአፍሪካ የሴቶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር እ.አ.አ በ1986 የተጀመረ ሲሆን የግብጹ አል አህሊ 10 ጊዜ፣ የኬንያው ኬንያ ፓይፕላይንስ ስድስት ጊዜ እንዲሁም ሌላኛው የኬንያ ክለብ ኬንያ ፕሪዝስንስ አምስት ጊዜ አሸንፈዋል።