ህዝበ ሙስሊሙ በፆሙ ወር በአንድነት ለሀገር ሰላምና ልማት የድርሻውን ለመወጣት የሚተጋበት ወቅት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ሙስሊሙ በፆሙ ወር በአንድነት ለሀገር ሰላምና ልማት የድርሻውን ለመወጣት የሚተጋበት ወቅት ነው
ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 06/2013(ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን የፆም ወር አንድነቱን ጠብቆ ለሀገር ሰላምና ልማት የድርሻውን ለመወጣት የሚተጋበት ወቅት መሆኑን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስታወቁ፡፡
የረመዳን ፆም የተቸገሩትን በመጠየቅና በመርዳት፣ ለራስና ለሀገር በፀሎትና በፍቅር ማሳለፍ እንደሚገባም ተመልክቷል፡፡
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ አህመድ አብደላ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ላይ እንደገለጹት፤ ህዝበ ሙስሊሙ ከሚከፋፍሉት ተግባራት በመራቅ አንድነቱን ጠብቆ ለሀገርና ለአካባቢው ሰላም መትጋት አለበት፡፡
“የረመዳን ፆም ራስን ለአላህ፤ ለፍቅር፤ለሰላም፤ለልማት የማስገዛት ወር ነው” ብለዋል፡፡
የረመዳን ወር በልማትና በዕድገት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም የሚታትርበት መሆኑን ገልጸው፤ ከስንፍናና ስራን ከመበደል በመራቅ ሁሉም በየተሰማራበት መስክ ውጤት ለማምጣት መትጋት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የምክር ቤቱ የመስጂድና የአውቃፍ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ ኢብራሂም ኢማም በበኩላቸው 1ሺህ 442ኛው የረመዳን ወር ፆም ሙስሊሙ ማህበረሰብ አንድነቱን ጠብቆ በሀገር ልማትና ሰላም ላይ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግብበት ይሆናል ብለዋል፡፡
በተለይ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ይዞ የሚመጣውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ዳር ለማድረስ ሙስሊሙ ህብረተሰብ እያደረገ የሚገኘው ድጋፍ በረመዳን ፆም ወቅትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮ የረመዳን ወር ፆም ለተቸገሩት መልካም ተግባራት የሚከናወንበትና ሰው ያለውን በፍቅር ተካፍሎ በአንድነት የሚያሳልፍበት የሰላምና የፀሎት ወር ነው ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ኢሊያስ አልይ ናቸው፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ኮሮና አሁንም የጤና፣ የማህበራዊና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ እያንዳንዱ ነዋሪ የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ በመተግበር ራሱን ፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን መጠበቅ አለበት፡፡