ቀጥታ፡

ለአፍሪካ አገሮች አምባሳደሮች በህዳሴ ግድብና በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ውዝግብ ዙሪያ ገለጻ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 5 ቀን 2013 (ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ እና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴሮች ለአፍሪካ አገሮች አምባሳደሮች በህዳሴ ግድብና በኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ውዝግብ ዙሪያ ገለጻ አደረጉ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ አገሮች በአፍሪካ ህብረት መሪነት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ላይ የተካሄደውን የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሶስትዮሽ ድርድርን የተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸው በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄደው ድርድር ኢትዮጵያ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ላይ እንዲደረስ አቋም እንዳላት አስታውቀዋል።

በአፍሪካዊነት ወንድማማችነት መንፈስ በመተባበር የአባይን ውሃ ማስተዳደርና መጠቀም የተሻለው አማራጭ እንደሆነ ሚኒስትሮቹ አስረድተዋል።

በሱዳንና በግብጽ በኩል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአረብ አገሮችና የተፋሰሱ አገሮች የውሃ ዋስትና ስጋት እንደሆነ በመግለጽ የሚያንጸባርቁት አቋም ትክክል እንዳልሆነም አብራርተዋል።

በመሆኑም እንዲህ ያለው የግድቡን የልማት ጉዳይ የፖለቲካ ቀለም እንዲይዝ ማድረግ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

ወሳኙና ሊያሰራ የሚችለው ስኬታማ የድርድር መንገድ በመጀመሪያው የውሃ አሞላል እና በሌሎች ተዛማጅ ስራዎች ላይ በመስማማት የአባይን ውሃ ለመጠቀም ሁሉን አቀፍ ስምምነት የሚያመጣ ሂደት ማስቀጠል እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በሚቀጥለው የክረምት ወቅት ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት ላይ መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠሯን የጠቀሱት ሚኒስትሮቹ፤ በጉዳዩ ላይ የሁለቱን አገሮች የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሮች እንዳገኘች ገልጸዋል።

ከግድቡ የድርድር ሂደት በተጨማሪ ለአምባሳደሮቹ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ስላለው የድንበር ውዝግብ ገለጻ ያደረጉት ሚኒስትሮቹ፤ ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጽኑ አቋም እንዳላት አስረድተዋል።

በገለጻው ላይ የተሳተፉ አምባሳደሮች ለተደረገላቸው ማብራሪያ አመስግነው፤ ‘የግድቡ ጉዳይ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ መፍታት በሚለው መርህ መሰረት መቋጨት እንዳለበት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ በሰላም ለመፍታት የምታደርገውን ጥረትም እንዳደነቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም