ቀጥታ፡

ዜጎች በዕርቅና መተሳሰብ ነባር አብሮነትን ማጠናከር ከቻሉ ሰላም ይመጣል- ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ

ሚያዚያ 5/2013 (ኢዜአ)  ዜጎች ዘርና ብሔር ሳይለዩ በዕርቅና መተሳሰብ ነባር አብሮነትን ማጠናከር ከቻሉ የሚፈለገው ሰላም እንደሚመጣ የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ ተናገሩ።

ግብረ ኃይሉ ከማንዱራ ወረዳ ገነተ ማርያም ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ ላይ ሌተናል ጀኔራል አስራት እንደገለጹት  ዜጎች መኖሪያቸውን ለቅቀው ወደ ሌላ አካባቢ መፈናቀል ሳይሆን አብሮነትን ማጠናከር ይገባቸዋል ።

ኮማንድ ፖስቱ የዞኑን ሰላም ለመመለስ ይሰራል፤ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የተጠናከረ የህግ ማስከበር ስራም ያከናውናል ነው ያሉት።

ማህበረሰቡም በውስጡ ያሉ የጥፋት ኃይል ተባባሪዎችን፣ ዘራፊዎችንና የጥይት ነጋዴዎችን ለኮማንድ ፖስቱ ማሳወቅ፤ እኩይ ድርጊቶችንም ማውገዝ አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ  ነዋሪዎች በበኩላቸው ማህበረሰቡ በሽፍታ ምክንያት ለዘርፈ-ብዙ ችግሮች ተጋልጧል ብለዋል። 

ቀደም ሲል በአካባቢው የሚኖር የሁሉም ብሄር ተወላጅ በመቻቻልና በጠንካራ አብሮነት ሕይወቱን ሲመራ እንደነበር አስታውሰው፤ ሽፍቶች በፈጠሩት ቀውስ ለችግር መዳረጋቸውንና የግብርና እንቅስቃሴያቸውን ማካሄድ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

ነዋሪው እርስ በርስ እንዲጋጭ የሚሰሩ አካላት እንዳሉም ጠቅሰው፤ ለዚህ ቀውስ የሚዳርጉ አካላት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይመጣ የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉ በመጠቆም፤ "የፖለቲካ ትርፍ ለሚሹ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳንሆን በር ልንዘጋ ይገባል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም