ቀጥታ፡

መራጮች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ካርዳቸውን በመውሰድ አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

ሚያዚያ 05/2013 (ኢዜአ) መራጮች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የምርጫ ካርዳቸውን በመውሰድ አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምርጫ አስፈጻሚዎች ጥሪ አቀረቡ።

የምርጫ ካርድ ለመውሰድ የመጨረሻዎቹን ቀናት መጠበቅ፤ በሚፈጠረው መጨናነቅ ምክንያት ለኮቪድ ወረርሽኝ ተጋላጭ ሊያደርግ እንደሚችልም አመልክተዋል።

የመራጮች የምዝገባ ቀን ሊጠናቀቅ 10 ቀናት ቀርተውታል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 6/2013 መሰረት አንድ መራጭ የሚፈልገውን ፓርቲ ወይም እጩ ተወዳዳሪ መምረጥ የሚችለው ቅድሚያ በመራጭነት ሲመዘገብ ብቻ ነው።

ለስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

ኢዜአ በአዲስ አበባ የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ ምልከታ አድርጓል።


የጣቢያዎቹ ምርጫ አስፈጻሚዎች እንደገለጹት በአንድ ምርጫ ጣቢያ 1 ሺህ 500 ሰው ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል።


ይሁንና ምዝገባው ከተጀመረ 20 ቀናትን ያስቆጠረ ቢሆንም ካርዱን እየወሰደ ያለው መራጭ እነርሱ በጠበቁት ልክ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

የምርጫ አስፈጻሚዎቹ ቤተመቅደስ አያሌው እና ውባለም ደረጄ በአንድ የምርጫ ጣቢያ የሚጠበቀውን ያህል ሰው እየመጣና እየተመዘገበ አለመሆኑን ገልጸው በቀሩት አስር ቀናት የሰዎች መጨናነቅ ይኖራል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ወጣት ኑረዲን ውቤ በበኩሉ የመራጮች ምዝገባ ቁጥር እንዲጨምር ምዘገባው ሊጠናቀቅ የቀረው ጊዜ  አስር ቀን መሆኑን የማስገንዘብ ስራ በመሰራቱ ከትናትና ጀምሮ የሰው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሷል።

በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ካርዳቸውን የወሰዱ መራጮች የመኖራቸውን ያህል በርካቶች ግን ''ይደርሳል'' በሚል እየወሰዱ አለመሆኑን የምርጫ አስፈጻሚዎች ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ካለው የኮሮና ስርጭት አኳያ መራጮች በጊዜ ካርዳቸውን በመውሰድ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን በመከላከል ረገድ አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በምርጫ ህጉ አንቀጽ 18 መሠረት አንድ ሰው በመራጭነት መመዝገብ የሚችለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሆነ፣ በምዝገባው እለት እድሜው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆነ እንዲሁም ለምዝገባ በቀረበበት የምርጫ ክልል ቢያንስ ለስድስት ወራት የኖረ ከሆነ ብቻ መሆኑ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በመላ አገሪቱ ድምፅ የሚሰጠባቸው 50 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች ያዘጋጀ ሲሆን፤ በእነዚህ ጣቢያዎች ከ152 ሺህ በላይ የመራጮች ምዝገባ የሚያካሂዱ ባለሙያዎችና ከ254 ሺህ በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች ማዘጋጀቱንም አስታውቋል። 

እስካሁን ባለው ሂደት በመላ አገሪቱ ምን ያህል መራጮች ካርድ ወሰዱ ብሎ ኢዜአ ለቦርዱ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ቦርዱ አጠቃላይ መግለጫ እንደሚሰጥበት ገልጿል።

በአዕምሮ ህመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌለው መሆኑ ስልጣን ባለው አካል ወይም በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠበት ሰው እንዲሁም የመምረጥ መብቱ በህግ ወይም አግባብ ባለው ህግ መሠረት በፍርድ ቤት ውሳኔ የተገደበበት ሰው በመራጭነት ሊመዘገብ አይችልም፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም