በአዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ከ430 በላይ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይቀርባሉ

52

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 5/2013 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ከ430 በላይ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚቀርቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ አስታወቀ።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተክሉ ሽኩር በጃንሜዳ የሚካሄደውን የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ከነገ ጀምሮ በጃንሜዳ በሚካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት በ18 ዘርፎች ከ430 በላይ የተለያዩ ችግር ፈች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይቀርባሉ ብለዋል።

በሳምንቱ የሚቀርቡት ዝግጅቶች የሰው ኃይልን ከማብቃት ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለመፍጠር ያስችላሉ ነው ያሉት።

በተጨማሪም ተቋማቱን ለማጥናት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል ሲዘጋጁ በነበሩት ኩነቶች ኢንተርፕራይዞች የተሻለ ምርት ይዘው እንዲቀርቡ መነሳሳት እንደፈጠረም አስታውሰዋል።

በመሆኑም ምርታማነትን የሚያሳድጉና በራሳቸው የሚተማመኑ ዜጎችን ለማፍራት ኤጀንሲው ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ።

"ሙያ ሃብት ነው'' በሚል መሪ ሃሳብ ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በሚከናወነው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም