ቀጥታ፡

ለ7 ቀናት የሚቆይ አገራዊ ጸሎትና ምህላ ታወጀ

ሚያዝያ 5/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሰባት ቀናት የሚቆይ የጋራ ሀገራዊ ጸሎትና ምህላ መታወጁን አስታወቀ።

ጉባኤው የጸሎትና ምህላ መርሃግብሩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

የጋራ መርሃ ግብሩ ሚያዝያ 7 ከቀኑ 9 ሰዓት በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በይፋ የመክፈቻ ስነ ሰርዓት ይደረጋል ተብሏል።

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው ጠቅላይ ፀሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት አገሪቱ ካለችበት ችግር ለመውጣት የጋራ ጸሎት ያስፈልጋል።

በአገሪቱ በተለይ ብሔርን መሰረት አድርጎ የሚፈጸም ግጭትና ግድያ እየተበራከተ መምጣት፣ የኮቪድ 19 ስርጭት መስፋፋት ፀሎትን ይሻል ብለዋል።

በተጨማሪም  አገሪቱ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት አለመግባባት የሃይማኖት አባቶች ስላሳሰባቸው የጸሎትና ምህላ አዋጅ እንዲታወጅ አድርገዋል ብለዋል።

ከሚያዚያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት የሚቆየው  የጸሎትና ምህላ መርሃ ግብር በቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች ይተላለፋል ብለዋል።

ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ንሰሃ መግባትና ከፈጣሪ ጋር መታረቅ ስለሚያስፈልግ ሁሉም ለአዋጁ መፈጸም ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በአይነቱ ልዩ የሆነው መርሃግብር "ከመሪ እስከ ተመሪ በዳይና ተበዳይ ይቅር የሚባባሉበትና በምድሪቱ የፈሰሰው ደም በንስሃ እንዲታጠብ ንስሃ የሚገባበት" መሆኑንም አብራርተዋል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የሚሰጠው  የትምህርት እንደ እስካሁኑ ቤተ እምነቶቹ በፈለጉት ሳይሆን ርዕሰ ጉዳይ ተመርጦ ለሁሉም በተመሳሳይ ይሰጣቸዋል ነው ያሉት። 

በዚህም መሰረት ዓርብ ስለ ንስሃና መጸጸት፣ ቅዳሜ ስለ ይቅርታና እርቅ፣ እሁድ ስለ ርሕራሔና እዝነት የሚሰበክ ይሆናል።

በተያዘው መርሃግብር መሰረት ሰኞ ስለ ተስፋ፣ ማክሰኞ ስለ እምነት፣ ረቡዕ ስለ ፍቅር፣ ሐሙስ ስለ ምስጋና ትምህርት ይሰጣል ተብሏል።

የፀሎትና ምህላው መክፈቻና መዝጊያ መርሃግብር በሰባት የመገናኛ  ብዙሃን በቀጥታ ስርጭት እንደሚኖረውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም