የጋራ እሴቶቻችን ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት ያላቸውን ጠቀሜታ ማጉላት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ እሴቶቻችን ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት ያላቸውን ጠቀሜታ ማጉላት ይገባል
ጎባ፣ ሚያዝያ 5/2013 (ኢዜአ) የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራዊ መግባባትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚያደርጉት ጠቀሜታ እንዲጎላ ዩኒቨርሲቲዎች በጥናትና ምርምር ሊደግፉ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አሳሰበ።
“የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራዊ መግባባትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ያላቸው ፋይዳ” በሚል መሪ ሀሳብ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባባር ያዘጋጁት 4ኛው ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት በባሌ ሮቤ እየተካሄደ ነው፡፡
በዐውደ ጥናቱ ላይ የጋራ እሴቶቻችንን ፋይዳ አጉልቶ የሚያሳዩ 13 ጥናታዊ ጽሁፎች ከሀገሪቷ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተጋበዙ ምሁራን ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡
በዐውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካይ ወይዘሮ ማሚት ይልማ እንዳሉት ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉና እንዲያስተሳስሩ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ስራዎችን ማከናወን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከዘርፉ ምሁራን ይጠበቃል።
ወይዘሮ ማሚት አክለውም ሚኒስቴሩ በየጊዜው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት አገራዊ ፋይዳ ባላቸውና ሴክተሩን የሚመለከቱ ጥናቶችን ለውይይት በማብቃት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ለውይይት የቀረቡት ጥናቶችም መንግስት በሚያወጣቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎች እንዲጠቀምበት አልሞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል በበኩላቸው ሀገራችን የበርካታ ባህሎች፣ እሴቶችና የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ብትሆንም ሀብቶቹን በአግባቡ ለይቶና አልምቶ ለሚፈለገው ጥቅም በማዋል ረገድ ውስንነቶች ይስተወላል” ብለዋል፡፡
የጋራ እሴቶች ተለይተውና ለምተው ለህብረ ብሔራዊ አንድነትና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲያበረክቱ በጥናትና ምርምር ለመደገፍ በትኩረት እንደሚሰራም አክለዋል፡፡
“ዶክተር አህመድ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ያዘጋጀው ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ የዚሁ ጥረት አካል ነው” ብለዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የተሳተፉት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አረጋዊ በርሔ በበኩላቸው በማህበረሰቡ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የመጡ እሴቶቻችንን በማጎልበት ለሀገራዊ ልማትና አንድነት ልናውላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
የታላቁ የህዳሴ ግድብ አንዱ የኢትዮጵያዊያኖች የጋራ እሴት፣ የአንድነትና የሉዓላዊነት መገላጫ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
ህዝቦቻችንን ከጨለማ ወደ ብልፅግና የሚያሻግረው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እስኪውል ድረስ ሁሉም ዜጋ ድርሻውን እንዲወጣም ዶክተር አረጋዊ ጥሪ አቅርበዋል።
"ኢትዮጵያዊያን ባላቸው የጋራ እሴቶች ተጠቅመው የሀገራቸውን ነፃነትና አንድነት አስከብረው ለዛሬ ደርሰዋል" ያሉት ደግሞ በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አንድነት በአንድ ጀምበር የሚፈርስ የሚመስላቸው ቡድኖች የኢትዮጵያዊያንን ስነ-ልቦናና የጋራ እሴቶችን ካለመረዳት የሚመነጭ እንደሆነም አመልክተዋል ፕሮፌሰሩ፡፡
ዕድር፣ ባህላዊ የፍትህ አሰጣጥ ስርዓት፣ ባህላዊ የስልጣን ሽግግር፣ ሃይማኖታዊ ስርዓቶችና በዓላት እንዲሁም ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚጋሯቸው የጋራ እሴቶች እንደሆኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚሁ በዓመታዊ የምርምር ጉባኤው ላይ የባሌ ዞን ባህላዊ ምግቦች አውደ ርዕይም የቀረበ ሲሆን በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ በዞኑ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች በታዳሚዎች እንደሚጎበኙም ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡