ቀጥታ፡

አምራች ኢንተርፕራይዞች ወደ ኢንዱስትሪው የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር በማገዝ በኩል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫቱ ተገለጸ

ሀዋሳ ሚያዝያ 05/2013 (ኢዜአ) አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በሀገር ደረጃ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በማገዝ በኩል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫቱ ተገለጸ።

ሀገር አቀፍ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በስልጠናው መድረክ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ  የአጭርና የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት ራዕይ ለማሳካት ጠንካራና ተወዳዳሪ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መገንባት ያስፈልጋል።

አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች የስራ ዕድል ፈጠራን ብሎም በሀገር ደረጃ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በማገዝ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዞች በሀገር ደረጃ የተጣለባቸውን ግብ እንዲያሳኩ ከዚህ በፊት ይገጥሟቸው የነበሩ የፋይናንስ፣ የመሠረተ ልማትና የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን በማቃለል ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም ለውጥ ማምጣት መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው ይህ ስልጠናም የዚህ አካል በመሆኑ ተሳታፊዎች  በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባዘጋጀው ስልጠና  ከደቡብ፣ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተውጣጡ  ከ300 የሚበልጡ ኢንተርፕራይዞች እየተሳተፉ ሲሆን ከትናንት ጀምሮ  ለአምስት ቀናት በሚያድረጉት ቆይታም በቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀት፣ ፋይናንስና ሰው ሀብት አስተዳደር፣እንዲሁም  ንግድ ሥራ አመራርና ገበያ ፍለጋ  ላይ ትምህርት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም