ቀጥታ፡

ኤምባሲው በጅቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መብትና ክብር ለማስጠበቅ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መብትና ክብር ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ኤምባሲው የዜጎችን መብትና ክብር ለማስጠበቅ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የሁለቱ አገሮች ሕዝቦችን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር ከጅቡቲ መንግሥት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል ምክክር መካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ገልጿል። በምክክር መድረኩ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ፣ የጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አብዱላሂ አብዲና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። በዚህ ወቅት አምባሳደር ሻሜቦ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያውያንን መብት ለማስጠበቅ ኤምባሲው ከአገሪቱ ብሔራዊ ፖሊስ እና ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ተወካዮች ጋር በጋራ እየሰራ ነው። ኢትዮጵያውያኑ በሕገ ወጥ መንገድ የጉዞ ሰነድ ሳይኖራቸው የጅቡቲ ድንበርን አቋርጠው በመግባት ለከፋ ችግርና ስቃይ እየተጋለጡ መሆኑንም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያውያኑ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስወገድ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የዜጎችን መብትና ክብር በማስጠበቅና በጅቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አዲስ በተከፈተው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ተወካዮች በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። የጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አብዱላሂ አብዲ በበኩላቸው በጅቡቲ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን የተለያዩ አደረጃጀቶች ከጅቡቲ መንግስትና ከኤምባሲው ጋር በመተባበር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል። ከመኖሪያ ፈቃድ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችን ለመፍታት እንደሚሰሩም ጠቁመዋል። የትውልደ ኢትዮጵያውያን ተወካዮች በጅቡቲ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከአገሪቱ የብሔራዊ ፖሊስና ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ መግለጫው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም