ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ጅማ አባጅፋር ዮሐንስ ሳህሌን አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል

አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ጅማ አባጅፋር ዮሐንስ ሳህሌን አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል። ክለቡ ዮሐንስን ለአንድ ዓመት በሚቆይ የኮንትራት ውል ማስፈረሙን የጅማ አባጅፋር ክለብ ስራ እስኪያጅና የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ ለኢዜአ ገልጸዋል። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከክለቡ ጋር የውል ስምምነቱን ዛሬ በይፋ እንደሚፈርምም ጠቁመዋል። ዮሐንስ ሳህሌ በዘንድሮው የውድድር ዓመት መቀሌ ከተማን በማሰልጠን አራተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ አድርጎታል። ጅማ አባጅፋርን የሊጉ አሸናፊ ያደረጉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ በቀጣይ ከመቀሌ ከተማ ጋር ድርድር እያደረጉ መሆኑንና መቀሌ ከተማ ቀጣይ ማረፊያቸው ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል። ከሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በኋላ በይፋ የተቀላቀሉበትን ክለብ እንደሚያሳውቁም ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ጅማ አባጅፋር የቀድሞውን የድሬዳዋ ከተማ ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር ዳምጠውን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አድርጎ ለመቅጠር መስማማቱንም አቶ መኪዩ መሐመድ ተናግረዋል። በያዝነው ሳምንት ውል ተፈራርመው በይፋ ስራቸውን እንደሚጀምሩም ጠቁመዋል። በተጫዋቾች ዝውውር ዜና ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ የደደቢቱን የግራ መስመር ተጫዋች ብርሃኑ ቦጋለና የጅማ አባጅፋሩን የመሐል ተከላካይ ቢኒያም ሲራጅ ማስፈረሙን የክለቡ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ነጋሲ መንገሻ ለኢዜአ ገልጸዋል። ሁለቱም ተጫዋቾች የአንድ ዓመት የኮንትራት ውል መፈራረማቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም የክለቡ አምበል በረከት ተሰማ ፣ ግብ ጠባቂው ዮሐንስ ሽኩር እንዲሁም የአማካይ ተጫዋቹ ዋለልኝ ገብሬና ተከላካዩ ተስፋዬ ዲባባ ከወልዋሎ ጋር ያላቸውን ቆይታ በአንድ ዓመት ማራዘማቸውን አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም