ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ካራቴ ስፖርት ሻምፒዮና በደሴ ከተማ ተጀመረ

ደሴ፣ ሚያዚያ 3/2013 (ኢዜአ ) በደሴ ከተማ አስተዳደር 110 ስፖርተኞችን ያሳተፈ የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ ተጀመረ።

ውድድሩ እስከ ሚያዚያ 7/2013 የሚቆይ ሲሆን 7 ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ እንደገለጹት ውድድሩ የካራቴ ስፖርቱን ለማሳደግ በህዝብ ዘንድ የተሻለ እውቅና እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ ነው።

እንዲሁም የእርስ በእርስ ግንኙነቱን ማጠናከርና በሰኔ ወር ለሚካሄደው የአፍሪካ ካራቴ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞችን መምረጥ ጭምር እንደሆነም ገልፀዋል።

"ውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች በተናጠልና በቡድን የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመው፤ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳዩ 15 ስፖርተኞችም ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ይመረጣሉ"ብለዋል፡፡

ወሎ የሰላም፤ የፍቅርና የአብሮነት ተምሳሌት በመሆኑ ለውድድር ቦታ መመረጡን ጠቁመው፤ ስፖርተኞች የወሎን ባህልና እሴት በአካባቢያቸው ማሳየትና ማስተማር ይጠበቅባቸዋል"ብለዋል።

የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዱኛ ይግዛው እንደገለጹት ውድድሩ የኢትዮጵያን ባህልና ወግ በሚያሳይ መልኩ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

"ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ስፖርተኞችም የአካባቢያቸውን ባህል ለሌሎች በማስተማር አንድነታቸውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል፡፡

አገር ከገባችበት ውስብስብ ችግር እንድትላቀቅም ስፖርት ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ "ስፖርተኞች በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሰላምና አንድነትን መስበክ ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡

የተሻለ ውጤት ለማምጣትና ኢትዮጵያን ወክለው በአፍሪካ ውድድር ለመሳተፍ ዝግጅት ማድረጋቸውን የተናገረው ደግሞ ከአማራ ክልል ተወዳዳሪዎች መካከል ወጣት ሳሊም ሁሴን ነው፡፡

"ውድድሩ አንድነትና ሰላማችንን ከማስጠበቁም ባለፈ የካራቴ ስፖርት እንዲጎለብትና ህብረተሰቡም እገዛ እንዲኖረው ያደርጋል" ብሏል፡፡

ሌላው አፋር ክልልን ወክሎ የሚሳተፈው ወጣት መሃመድ ኢሴ በበኩሉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ልምምድ ማድረጉን ተናግሯል።

"አገራችን ከአፍሪካም የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ በቅንጅት እንሰራለንም" ብሏል፡፡

በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ከፌዴራል፤ ከክልልና ከደሴ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ አመራሮች፤ የስፖርት ቤተሰቦችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም