ቀጥታ፡

"ፍቅር ያሸንፋል" ማህበር ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3/ 2013 ( ኢዜአ) የ"ፍቅር ያሸንፋል" ማህበር ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ማህበሩ በኮልፌ ቀራኒዮ የሚገኘው የሙስሊም መካነ-መቃብር በመገኘት አካባቢውን የማጽዳት ስራ አከናውኗል።

የማህበሩ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሚስባህ ከድር እንዳሉት የመቃብሩ ስፍራ ጫካ በመሆኑ ጅብ እየወጣ የአካባቢውን ነዋሪ ይተናኮል ነበር።

በመሆኑም የማህበሩ አባላት ከሌሎች ነዋሪዎች ጋር በመተባበር አካባቢውን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ማጽዳት መቻሉን አብራርተዋል።

የማህበሩ አባላት ቀደም ሲል የጥምቀት በዓል የሚከበርበትን ቦታ ማጽዳታቸውን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ  በተመሳሳይ የኢድ በአልም ሲከበር ለማፅዳት ተዘጋጅተናል ብለዋል።   

ማህበሩ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት ጋር በተያያዘም በተለይም ኮሮና በተከሰተበት ወቅት አቅም የሌላቸውንና ጠያቂ የሌላቸው ወገኖችን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አክለዋል።  

ከዚህ ቀደም ለጎዳና ተዳዳሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ከስምንት በላይ አቅመ ደካማ ቤቶችን የማደስ ተግባራትንም አከናውኗል ብለዋል።  

በጽዳት መርሃ ግብሩ ከተሳተፉት መካከል ዓለማየሁ ታደሰ የማህበሩ አባል ሲሆን "እኔ ክርስቲያን ነኝ እንደዚህ ዓይነት በጎ ተግባራት ላይ መሳተፍ ፍቅርን መታሳሰብን ለማጠናከር ወሳኝ በመሆኑ ተሳትፌያለሁ" ብሏል።   

ወጣት ቡልቻ አባኑራ በበኩሉ ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ሃይማኖት ቢኖረንም አንድነታችንን ለማሳየት እዚህ ተገኝተናል ብሏል።   

"ያለን አገር አንድ ነው፤ ለመጪው ትውልድ አንድነቷ የተጠበቀ አገር ለማስረከብ ጥላቻን ሳይሆን ሰላምን፣ ፍቅርንና አብሮነትን ማጠንከር ይገባናል" ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።    

የማህበሩ አባላት መካነ መቃብሩን ከማጽዳት ጎን ለጎን የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስም ቃል ገብተዋል።

ማህበሩ በውጭም በአገር ውስጥም ከአስር ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን የብሄርና የሃይማኖት ገደብ የሌለው አንድነትንና ወንድማማችነት ለማጠናከር ዓላማ አንግቦ የተነሳ መሆኑን ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

"ፍቅር ያሸንፋል" ማህበር ከ10 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን ከዘር፣ ከሃይማኖት እንዲሁም ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር የማይወግን "ሰው" መሆንን ብቻ መሰረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም