የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመቄዶንያ 100 ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ካርታ አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመቄዶንያ 100 ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ካርታ አስረከበ
ሚያዚያ 3/ 2013 ( ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር ለመቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በድሬዳዋ ከተማ የ100 ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ካርታ አስረከበ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር እና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች በአዲስ አበባ የሜቄዶንያ መርጃ ማዕከል በመገኘት የቦታውን ካርታ አስረክበዋል።
ምክትል ከንቲባው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የሜቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የሀገር ባለውለታ ተቋም ነው።
ማእከሉ ዘር ሃይማኖትና ቋንቋ ሳይገድበው በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በመገኘት ጎዳና ላይ የወደቁትን ዜጎች አንስቶ ለክብር የሚያበቃ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ማእከል ድጋፍ እና አጋርነታችንን ማሳየታችን እንዳለ ሆኖ 100 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥተናል ብለዋል።
"አስተዳደሩ ያበረከተው የመሬት ካርታ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም" ያሉት ምክትል ከንቲባው በቀጣይም የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ እንዲሁም ለማዕከሉ የንፅህና መጠበቂያና ሌሎች ቁሳቁስ ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙንኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ህዝቅያስ ታፈሰ በበኩላቸው መቄዶንያን በድሬ ቲቪ እንዲሁም በድሬ ኤፍ ኤም ነፃ የአየር ሰዓት ሰጥተን የሚሰራውን በጎ አላማ ለህዝብ እናስተዋውቃለን ብለዋል።
የመቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ቢንያም በለጠ የማዕከሉን አላማ ተረድተው ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፤ ለውለታችሁ ፈጣሪ ዋጋችሁን ይክፈላችሁ ብለዋል።
የተቸገሩትን መርዳት ዋጋው ከፍ ያለ በመሆኑ ሌሎችም ተቋማት የድሬዳዋ አስተዳደርን መልካም አርአያነት እንዲከተሉ ጠይቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎችን እንደሚያስተናግድ ገልጸው ተጨማሪ ስድስት ሺህ ሰዎችን ለመቀበል ያቀደውን ግብ እውን ለማድረግ በቅርቡ 300 ጎዳና ላይ የወደቁ ሰዎችን ያነሳል ብለዋል።
በአዲስ አበባ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማእከሉ የሚያስገነባውን የህንጻ ግንባታ ለማጠናቀቅ በቀጣይ የሁሉም ድጋፍና እገዛ እንዲታከልበት ጠይቀዋል።