ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈፀመውን ጥቃት የትግራይና አማራ ክልል መንግስታት አወገዙ - ኢዜአ አማርኛ
ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈፀመውን ጥቃት የትግራይና አማራ ክልል መንግስታት አወገዙ
መቀሌ ሀምሌ 23/2010 የትግራይና የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት ይሰሩ በነበሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዙ፡፡ በፕሮጀክቱ ይሰሩ በነበሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ በደረሰው ጥቃት ሶስት ንጹሀን ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትም በድርጊቱ የተሰማውን ሀዘን በመግለፅ፣ ጉዳዩን አጣርቶ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ ወደ ስፍራው የአመራርና ባለሙያዎች ቡድን መላኩን አስታውቋል። በአማራ ክልል ጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት ላይ ይሰሩ በነበሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰው ጥቃት ህገ መንግስታዊ መብትና የሰዎች ነጻነትን የሚገፋ መሆኑን በመግለጽ አውግዘዋል፡፡ "የሀሳብ ልዩነት ካለ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መግለጽ እየተቻለ ዘርን በመለየት የሚደረገው ጥቃት በማንኛውንም መለኪያ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም "ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግስት በዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት መሪር ሀዘን እንደተሰማውና ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ በዜጎች ላይ ጥቃት ያደረሱ ግለሰቦች ወደ ህግ እንዲቀርቡ የፌደራልና የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ወደ ህግ በማቅረብ አስተማሪ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል፡፡ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ወደ አካባቢው ቡድን በመላክ ዝርዝር መረጃ ለማቅረብ ጥረት እንደሚያድርግ ጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት በአማራ ክልል በለስ ስኳር ፕሮጀክት በዜጎች ላይ በደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግስት የተሰማውን ሀዘን ይገልጻል ፤ ጉዳዩን አጣርቶ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብም ወደ ስፍራው የአመራርና ባለሙያዎች ቡድን ልኳል። በክልሉ ውስጥ የዜጎችን ማንነት መነሻ አድርጎ የሚደርስ ጉዳትም ሆነ ማንኛውም ጥቃት የክልሉ መንግስት አምርሮ እንደሚያወግዝና እንደሚታገለው የቢሮው ኃላፊ አቶ ንጉሱ አስታውቀዋል።