ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ ክህሎት ውድድርና ሲምፖዚየም በደሴ ከተማ ተጀመረ

63

ባህር ዳር ሚያዚያ 2/2013 ( ኢዜአ ) በአማራ ክልል ለሰባተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ ክህሎት፣ ተግባራዊ የምርምር ውድድርና ሲምፖዚየም በደሴ ከተማ ተጀመረ።

ዝግጅቱ ለአምስት ቀናት በሚያደርገው ቆይታ 138 አሰልጣኞችና ሰልጣኞች ተወዳድረው የሚያሸንፉት በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ተመሳሳይ መረሃ ግብር እንደሚሳተፉ  ተገልጿል።

በተጨማሪም በኢንተር ፕራይዞች፣ አንቀሳቃሾችና ሌሎች የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ተወዳድረው ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡትም ዕውቅና እንደሚሰጥ ተመልክቷል።

የክልሉ ቴክኒክ ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አቶ ድረስ እሸቱ እንደገለጹት፤ ሀገሪቱ  ከጥንት ጀምሮ በቴክኒክና ሙያ ጥልቅ ዕውቀት እንደነበራት የታሪክ አሻራዎች ያመለክታሉ።

ይሁን እንጂ በሂደት የመጡ መንግስታት የቴክኒክ ዕውቀትን ቢያጣጥሉትም አሁን ላይ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በርካታ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በክልሉ ተቋቁመው የልማቱ ደጋፊ የሰው ሃይል እያፈሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

መንግስት ያስቀመጠውን የቴክኖሎጂ ኩረጃና ማላመድ ተግባር በአግባቡ በመከወን የብልጽግናው ጉዞ ለማቀላጠፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሲምፖዚየሙም የዘጠኝ ወራት የዘርፉ ዕቅድ አፈፃጸም ቀርቦ ውይይት በተሳታፊዎች እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም