ቀጥታ፡

ፓርቲዎች የተመደበላቸውን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ በአግባቡ መጠቀም አለባቸው - መገናኛ ብዙሃን

ሚያዚያ 2 /2013 (ኢዜአ) የመጪው አገራዊ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን ለማስተዋወቅ የተመደበላቸውን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ በአግባቡ እንዲጠቀሙ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አስገነዘቡ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎች ለምርጫው ሠላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊነት ፓርቲዎችን በእኩልነት ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የጽህፈት ቤት ኃላፊና የተቋሙ የምርጫ ዴስክ አባል አቶ አዳም ታደሰ ተቋማቸው ምርጫ ቦርድና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በደለደሉት የአየር ሠዓት መሰረት ሁሉንም ፓርቲዎች በፍትሃዊነት ለማገልገል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

በቀደሙት ምርጫዎች ከገዢውና ከጥቂት ፓርቲዎች በቀር አብዛኞቹ የተመደበላቸውን የአየር ሠዓት በአግባቡ ሲጠቀሙ እንዳልነበረ አስታውሰዋል።

በመጀመሪያ ቀን ያመጡትን የምርጫ ቅስቀሳ እስከ መጨረሻው እንዲደጋገም መጠየቅ፣ የተሰጣቸውን የአየር ሠዓት አለማስታወስ፣ የተደራጀ መረጃ ያለማምጣትና ሌሎች ክፍተቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች ካለፉት ስህተቶች በመማር የተመደበላቸውን የአየር ሠዓት በአግባቡ እንዲጠቀሙ አቶ አዳም መክረዋል።

የአየር ሠዓታቸውን አንዱ ሌላውን በመተቸት ከማባከን ይልቅ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በምጣኔ ሃብት ዘርፎች ያሏቸው አማራጭ ሃሳቦች ላይ ትኩረት አድርገው መልዕክት በማስተላለፍ እንዲጠቀሙበትም አስገንዝበዋል።

የመልዕክት ቀረጻን በተመለከተ እገዛ ለሚሹ ፓርቲዎች ተቋማቸው አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የአሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ መገናኛ ብዙሃን ከዚህ ቀደም የተካሄዱ አምስት ምርጫዎችን ጥንካሬና ድክመት በማጥናት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ክርክር ሙያዊ ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ለማስተናገድ ተቋማቸው ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፓርቲዎቹ በሚያደርጓቸው ክርክሮች ባለፉ ሁነቶች ላይ ከመቆዘም፣ ሕዝብን ለአመጽና ለበቀል ከማነሳሳት ወጥተው ለሕዝብ ሊሰሩ ባሰቧቸው ተግባራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሳይወግን እኩል አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የድርጅቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፈቃዱ ከተማ ተናግረዋል።

"ይህም ምርጫው በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን ፋይዳው የጎላ ነው" ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ሙያተኞች ከምንም በላይ አገርን በማስቀደም ምርጫው ፍትሃዊ፣ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ኃላፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

በየተቋሞቻቸው ጋዜጠኞች ሙያን መሰረት ባደረገ መልኩ መረጃዎችን እንዲያሰራጩ በምርጫ ዘገባ ላይ ያተኮሩ የስራ ላይ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነም ገልጸዋል።


በስድስተኛ አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተመደበላቸው የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ የምረጡኝ ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም