የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚመጡ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል የተደራጀ ስልት መቀየስ ይገባል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚመጡ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል የተደራጀ ስልት መቀየስ ይገባል - ምሁራን
ሚያዚያ 2/2013 (ኢዜአ) ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ የሚመጡ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል የተደራጀ ሥልት መቀየስ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት እየተካሄደ ያለውን ድርድር አጠናክራ መቀጠል እንዳለባትም ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ምሁራን እንደተናገሩት፤ ግድቡን በተመለከተ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚመጡ ተጽዕኖዎችን በተደራጀ መልኩ መከላከል ይገባል።
በተለይም አስቀድሞ የቢሆን ትንታኔዎችን በመሥራት ከወዲሁ የአገርን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ መዘጋጀትና መንቀሰቀስ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሣሙኤል ተፈራ፤ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ አቋሟን ይበልጥ ማስተዋወቅ እንዳለባት ይናገራሉ።
እስካሁን ባለው ሂደት በተለያዩ ተቋማት በተናጥል በተሰሩ ስራዎች የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ቋንቋዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ያደረጓቸው ጥረቶች አበረታች መሆናቸውንም ነው የጠቀሱት።
ይሁንና ግድቡን በተመለከተ በተቋማትና በግለሰቦች የሚሰራጩት መረጃዎች ተናጥላዊ ሳይሆኑ በተደራጀ መልኩ መከናወን እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።
መረጃዎቹ የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ለሚያሰራጯቸው የተዛቡ መረጃዎች ማምከኛ ብቻ መሆን እንደሌለባቸውም ጨምረው ገልጸዋል።
በመሆኑም በተቋማት፣ በመገናኛ ብዙሃንና በግለሰቦች የሚወጡ መረጃዎችን ተቋማዊ ቅርጽ በማስያዝ አጀንዳ የሚሰጡ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የውሃ ሃብት ባለሙያው ፈቅ አህመድ በበኩላቸው የታችኛው የተፋሰስ አገራት በግድቡ ግንባታ ላይ የያዙት ትክክለኛ ያልሆነ አቋም ግድቡን ጨምሮ በናይል ተፋሰስ ጉዳዮች እንከን እየፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።
ለአብነትም የሱዳንና የግብጽ መርህን መሠረት ያላደረገ አካሄድ ለበርካታ ዓመታት በተሰራበት የናይል የትብብር ማዕቀፍ ላይ እንቅፋት የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻር በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደው ድርድር እንዳይሳካ የሚያደርጉትን ጥረት ኢትዮጵያ በተደራጀ አኳኋን መመከት እንደሚገባት ጠቁመዋል።
የታችኛው ተፋሰስ አገራት ተጽዕኖ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ተጽእኖውን በተደራጀ መረጃና አካሄድ ከወዲሁ መቋቋም ይገባል ነው ያሉት።
ከቀናት በፊት በአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀ-መንበር የኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሼሴኬዲ በተመራውና በኪንሻሳ በተካሄደው የሦስቱ አገራት ስብሰባ ኢትዮጵያ በኅብረቱ የሚካሄደው ድርድር እንዲቀጥል አቋሟን ዳግም መግለጿ ይታወሳል።