በምርጫው የሚበጃቸውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያበቃቸውን ካርድ እየወሰዱ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው የሚበጃቸውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያበቃቸውን ካርድ እየወሰዱ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ
ሀዋሳ፣ ሚያዚያ 2/2013 (ኢዜአ) በግንቦት ወር በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያበቃቸውን ካርድ እየወሰዱ መሆናቸውን በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በሀዋሳ መናኸሪያ ክፍለ ከተማ ቴሶ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያ ሁለት ካርድ ሲወስዱ የነበሩት ወይዘሮ ስንዱ ዘውዴ እንዳሉት፤ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸው ይበጀኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ያስችላቸዋል።
"ነገ ላይ ሌላው በመረጠው ከመተዳደርና ከማማረር አስቀድሞ እያንዳንዱ ግለሰብ የምርጫ ካርድ በመውሰድ የሚፈልገውን ፓርቲ የመምረጥ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት" ብለዋል።
ሀገራዊ አንድነትና ሰላም ለማምጣት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖርና የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚሰራ ፓርቲ ምርጫቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
በአዲስ ክፍለ ከተማ ዳካ ቀበሌ ቼመንታል መንደር ቁጥር ሶስት ጣቢያ ካርድ በመውሰድ ላይ የነበሩ ወይዘሮ ሰዓዳ አብደላ በበኩላቸው፤ ህግ አክብሮ የሚሰራ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያበቃቸውን ካርድ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ምርጫ እያንዳንዱ ዜጋ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም በጊዜው ተመዝግቦ ካርዱን መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል።
መራጮች በተፈለገው ልክ ካርድ እየወሰዱ እንዳልሆነ የተናገሩት ደግሞ በሀዋሳ መናኸሪያ ክፍለ ከተማ ቴሶ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያ ሁለት አስፈፃሚ ወይዘሪት ሰላማዊት ዘውዴ ናቸው።
ምዝገባ ከተጀመረ ካለፉት 15 ቀናት ወዲህ 42 ሰዎች ብቻ ካርድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው ይመዘገባል ተብሎ ከሚጠበቀው አንፃር ቁጥሩ አነስተኛ በመሆኑ መራጮች ከወዲሁ በመመዝገብ ካርድ መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ የሀዋሳ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ፋንታሁን ሀጢሶ በሰጡት አስተያየት ምርጫው ተአማኒ ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራን ነው ብለዋል።
የዘንድሮ ምርጫ እስካሁን ከተካሄዱት አንጻር መንግስት ትኩረት የሰጠውና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።
የበጀትና የተሽከርካሪ እጥረት ቢኖርባቸውም ደጋፊዎቻቸው የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ የምርጫ ህግና ደንቡ በሚፈቅደው መሰረት ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አንፃር ወደ መጨረሻ አከባቢ የሚፈጥረውን መጨናነቅ ለማስቀረት ዜጎች በሚቀርባቸው ጣቢያ በመገኘት የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
ምርጫው ፍፁም ተአማኒነትን ያተረፈ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የሀዋሳ ከተማ ሀላፊ አቶ ካሱ አሩሶ ናቸው።
ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲ ለሃገሪቱና ህዝቦቿ ደህንነት፣ ሠላምና ልማት ቅድሚያ አጀንዳ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመው ብልጽግና በከተማዋ ከሚንቀሳቀሱ 12 ፓርቲዎች ጋር የጋራ ምክር ቤት በማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የመራጮች ካርድ በተፈለገው ልክ ዜጎች እየወሰዱ ያለመሆናቸው የተናገሩት አቶ ካሱ ለዚህም የቅስቀሳ ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።