ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ለነዋሪዎች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተጨማሪ ሆስፒታሎች ያስፈልጓታል - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ

ሚያዚያ 2 / 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ ከሕዝብ ብዛቷ አንጻር የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተጨማሪ ሆስፒታሎች እንደሚያስፈልጓት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከሮሃ ሕክምና ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ብሩክስ ዋሺንግተንና ከሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ለሮሃ ሕክምና ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በመዲናዋ በተለምዶ ገርጂ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገነባው የሮሃ ሕክምና ማዕከል የአሜሪካው የኢንቨስትመንት ተቋም ሮሃ ግሩፕ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ የራሱ ወጪ ነው።

የሕክምና ማዕከሉ የንቅለ ተከላና ካንሰር ሕክምናን ጨምሮ በዘመናዊ የቀዶ ሕክምና ላይ ትኩረት የሚያደርጉ 1 ሺህ 100 አልጋዎችን የያዙ አምስት ሆስፒታሎች በመያዝ የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።

ሆስፒታሎቹ የልብ፣ የነርቭና የጀርባ እንዲሁም የሴቶችና ህጻናት ሕክምና አገልግሎቶች የሚሰጡ ናቸው።

የሕክምና ማዕከሉ የሜዲካል ትምህርት ቤት፣ የጥናትና ፈጠራ፣ የማገገሚያና የስልጠና ማዕከላትን በውስጡ ያካትታል።

የሕክምና ማዕከሉ ለሕዝብ ክፍት የሆነ የመዝናኛ ፓርክ የሚኖረው ሲሆን ከአምስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

የዚህ የሮሃ ሕክምና ማዕከል መሰረተ ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መንግስት አዲስ አበባን የሚያስተሳስሩ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

"መዲናዋን ለማስተሳሰር በሚከወኑ ስራዎች ክፍተት የነበሩት ሆስፒታልና የጤና አገልግሎት ተቋማት በመሆናቸው የሮሃ ሕክምና ማዕከል ግንባታ በዚህ ረገድ የሚኖረው ሚና ወሳኝ ነው" ብለዋል።

አዲስ አበባ ካላት የሕዝብ ብዛትና መዳረሻነት ለነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ተጨማሪ ሆስፒታሎች በብዛት እንደሚያስፈልጓትም አመልክተዋል።

በየዓመቱ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት በሕክምና ዘርፍ የሚመረቁ ተማሪዎችን ስራ የሚቀጥሩ የሕክምና ተቋማት መስፋፋት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

የሮሃ ሕክምና ማዕከል ግንባታ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ እንዳለበትና መንግስት በዚህ ረገድ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የገለጹት።

ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በሚከናወኑ የጤና ዘርፍ ስራዎች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው "የሮሃ ሕክምና ማዕከል ዜጎች ሕክምና ለማግኘት ወደ ውጭ አገር ሄደው የሚያወጡት የውጭ ምንዛሬ እንዲቀንስ ያደርጋል" ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በተመሳሳይ የጤና ተቋማት ግንባታ ላይ መሳተፍ የሚሹ ባለሀብቶች እንደሚያበረታታና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

የሮሃ ግሩፕና የሮሃ ሕክምና ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ብሩክስ ዋሺንግተን ማዕከሉ ለአገር ውስጥ ታካሚዎች አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ሆቴሎች ጋር በመስራት ለውጭ አገር ታካሚዎች የጉዞ ፓኬጆች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

ይህም ኢትዮጵያን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የሕክምና ማዕከሉን ግንባታ በአምስት ዓመት ለማጠናቀቅ መታቀዱንና በየዓመቱም አንድ ሆስፒታል ገንብቶ ወደ ስራ ለማስገባት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

መንግስት ለማዕከሉ ግንባታ እውን መሆን ላደረገው ድጋፍ ሚስተር ብሩክስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም