ቀጥታ፡

ለትግራይ ክልል የሚያስፈልገውን የሰብዓዊ እርዳታ ለሁለተኛው ዙር ለማቅረብ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ወደ ስራ ተገብቷል…አቶ ደመቀ መኮንን

ሚያዝያ 1/2013(ኢዜአ) ለትግራይ ክልል የሚያስፈልገውን የሰብዓዊ እርዳታ ለሁለተኛው ዙር ለማቅረብ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ወደ ስራ መገባቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መሪ ሚስተር ፔካ ሀቪስቶ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ትግራይ ክልል የሚያስፈልገውን ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የኢትዮጵያ መንግስት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍን መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን ለ4.5 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን አቶ ደመቀ አስታውሰዋል።

ለሁለተኛው ዙር የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትም ተገቢው የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ወደ ስራ መገባቱንም አብራርተውላቸዋል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ እርዳታው  ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎች ተለይተው ከመከላከያ ጋር በመተባበር የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአካባቢዎቹ የተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በክልሉ ቀደም ሲል ሲተገበር የነበረው የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም የተጀመረ መሆኑንና ይህም በክልሉ ሁኔታዎች ወደ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሱ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት።

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ ከማደረግ አንጻር የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቀደም ሲል በማይካድራና በአክሱም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ በማድረግ ያቀረበውን ሪፖርት አስታውሰው፣ በመንግስት በኩል በገለልተኛ አካላት ምርመራ እንዲደረግ ያለውን ቁርጠኝነት ያመላክታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ተቋም ጋር የጋራ ምርመራ ለማካሄድ ከስምምነት ላይ ተደርሶ በሂደት ላይ መሆኑንን አቶ ደመቀ ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ መንግስት በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነትም በማረጋገጥ፤ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተሳተፉ አካላት በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና በጠቅላይ አቃቤ ህግ በኩል አስፈላጊው ምርመራ በማድረግ በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ለልዑኩ ገልጸውላቸዋል።

ሚስተር ፔካ ሀቪስቶ በበኩላቸው ከሁለት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ተደራሽነትና የሚዲያ አካላት በክልሉ በመገኘት እንዲዘግቡ ከማድረግ አንጻር በመንግስት የተከናወኑ ተግባራት በአዎንታዊነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ያደረጉት ጉብኝትም ይህንን የሚያረጋግጥ መሆኑን በማስታወስ፤ ግጭተ ያለባቸው የተወሰኑ አካባቢዎች እርዳታ የሚያስፈለጋቸው ዜጎች ተገቢው እርዳታ እንዲደርሳቸው ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

አያይዘውም የአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች በክልሉ ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለተደራሽ አካላት ተገቢው ድጋፍ ማቅረብ እንዲቻል የፍላጎት አጠቃላይ ዳሰሳ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ እንዲሚወጣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መግለጻቸው በአዎንታዊነት እንደሚገነዘቡት ገልጸው፣ ሂደቱ እንዲፋጠን ጠይቀው፤ በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር እንደሚስፈልግ ገልጸዋል።

በመንግስት በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ከመጪው የዝናብ ወቅት በፊት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም እንዲቻል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል  አቶ ደመቀ አስታውቀዋል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የኤርትራ ወታደሮች አንደሚወጡ በገለጹት መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሂደቱ እንዲፋጠን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት በወንጀል ከተሰማሩ የተለዩ ዋና የህወሓት ቅሪቶች ውጭ ሌሎች አካላት በፈቃደኝነት ለመንግስት እጅ እንዲሰጡ የምህረት ገደብ ማውጣቱ አስታውሰው፣ በዚሁ መሰረት እጃቸውን ለመንግስት ያልሰጡትን ወደ ህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ አካላት ምክክር በማድረግ ህዝቡ የመፍትሔው አካል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ሚስተር ፔካ ሀቪስቶም መንግስት ከተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ አካላት ጋር ምክክር እንዲያደርጉ መታቀዱ በአዎንታዊነት እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተም ኢትዮጵያ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ድርድሩ በውጤት አንዲጠናቀቅ ላደረጉት ጥረት ከበሬታ ያላት መሆኑንም አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

በቀጣይም በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸውላቸዋል።

በተጨማሪም ድርድሩ በአውሮፓ ህብረት፣ በአሜሪካ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ታዛቢነት እንደሚካሄድ አብራርተውላቸዋል።

በኢትዮጵያ በኩል በውሃ ክፍፍል ስምምነት በሶስቱ አገራት መካከል ብቻ የሚካሄድ አለመሆኑና ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ገልጸው፣ ድርድሩ በግድቡ የውሃ ሙሌት ላይ ማተኮር እንዳለበት ክቡር አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

ሚስተር ሀቬስቶ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ድርድር ከመጪው ክረምት ከሚከናወነው የውሃ ሙሌት በፊት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ በአውሮፓ ህብረት በኩልም የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብን ሁለቱ አገራት በድርድር መፍታት ያለባቸው መሆኑን አንስተዋል።

አቶ ደመቀ በበኩላቸው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዑላዊ መሬት በወረራ መያዟን ተከትሎ ማውገዝ የሚጠበቅበት ቢሆንም ይህንን አለማድረጉ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ በኩል ችግሩ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ ጽኑ አቋም እንዳለ ማስረዳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም