ቀጥታ፡

መንግስት እና በሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አካላት ሁሉ ለሀገርና ለዜጎች ደህንነት ቅድሚያ እንዲሰጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ ሰላምና ሉዓላዊነት እንዲሁም ለዜጎች ደህንነት መንግስት እና በሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አካላት ሁሉ ቅድሚያ ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አሳሰበች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ሌሎች ብጹአን አባቶች በተገኙበት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በመግለጫውም መንግስት እና በሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አካላት ሁሉ ለአገር ሰላም፣ ሉዓላዊነት እንዲሁም ለዜጎች የህይወት ዋስትና መረጋገጥ ከምንም በፊት ቅድሚያ እንዲሰጡ ተጠይቋል።

ቤተክርስቲያኗ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የዘላለማዊ ህይወት መማጸኛ በመሆኗ ለዜጎች መልካም አኗኗር፣ ለአገር ሰላምና አንድነት፣ በጸሎት፣ በምህላ፣ በትምህርትና በማህበራዊ ተልዕኮ የድርሻዋን እየተወጣች እንደምትገኝ ተገልጿል።

ዜጎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ በሚያጋጥማቸው ወቅትም ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ሰብዓዊ እርዳታ፣ ትምህርትና መንፈሳዊ ማጽናኛ እያደረገች ነው ተብሏል።

የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸኃፊ እና የሲዳማና የጌዲኦ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ፤ በመግለጫቸው ከምንም በላይ የሃገርና የዜጎች ደህንነት ጉዳይ ይቅደም ብለዋል።

"መንግስት እና በሀገር ጉዳይ ያገባናል የምትሉ አካላት በሙሉ ለሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት፣ ለህዝብ አንድነትና መተሳሰብ፣ ለዜጎች ሁለንተናዊ ደኅንነትና የህይወት ዋስትና ቅድሚያ መስጠት አለባችሁ" ብለዋል።

ችግሮች ቢኖሩም እንኳን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን እያጡ ያሉ ንጹኃን ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ቀጣይ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቅስቀሳው እስከ ፍጻሜው ሂደቱን ሰላማዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፍጻሜ በመረባረብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሁሉም አካባቢዎች ንብረት ለወደመባቸው፣ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉና ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ሁሉ አቅም የፈቀደውን ሃይማኖታዊና ወገናዊ ድጋፍ እንዲደረግም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ በመምጣቱ ካህናትና ምእመኑ በቤተክርስቲያንም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

"በሰው ልጅ ላይ አሰቃቂ መከራን ማድረስ ውጤቱ ከድርጊቱ የባሰ መሆኑን በመገንዘብ፣ የሰው ህይወት ተከፍሎ የሚሳካ ማንኛውም ምድራዊ ፍላጎትና ዓላማ ጠባሳው ለትውልድ ነውና በአስተዋይ አእምሮ ለሀገራችን እና ለሕዝባችን በማሰብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የሰላም ጥሪያችንን እናስተላለፍለን" ብለዋል ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ።

ቤተክረስቲያኗ ከሌሎች የኃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ለአገራዊ ሰላም፣ ልማትና እድገት፣ ለዜጎች ሁለንተናዊ ደህንነት የበኩሏን ኃላፊነት እየተወጣች ሲሆን በቀጣይነትም አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም