ቀጥታ፡

ከመጪው ምርጫ ጋር ተያይዞ የዜጎች መብቶች እንዳይጣሱ ሲቪክ ማህበራት ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፣ ሚያዝያ 01/2013 (ኢዜአ) ከመጪው ምርጫ ጋር ተያይዞ የዜጎች የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዳይጣሱ ሲቪክ ማህበራት ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።

በሀገሪቱ የሚካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊና የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችን ያማከለ እንዲሆን ሲቪክ ማህበራት ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በሀዋሳና አካባቢው ለሚኖሩ ሲቪክ ማህበራት ስለምርጫውና ዜጎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ በማስመልክት ሥልጠና እየሰጠ ነው።

በሥልጠናውመድረክ  የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተር አቶ መስኡድ ገበየሁ እንዳሉት፤ የሲቪክ ማህበራት ከቅድመ እስከ ድህረ ምርጫ ወቅት ያሉ ሂደቶችን በንቃት መታዘብ ይጠበቅባቸዋል።

በተለይ  ዜጎች መብትና ግዴታዊቻቸውን በሚገባ ተረድተው በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከማንቃት ባለፈ ምርጫው ሠላማዊና የዜጎች ሰብዓዊ መብትን ያማከለ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄደው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭቶችና አለመግባባቶች በተበራከቱበት ወቅት ነው ያሉት አቶ መስኡድ ይህ ሁኔታ ከምርጫው ሂደት ጋር ተደምሮ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዳይጣሱ ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዜጎች በነፃነትና እኩልነት መሳተፍ እንዲችሉ አባላቶቻቸውንም ሆነ ማህበረሰቡን የማስገንዘብ ኃላፊነትም እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማስቻል ህብረቱ ከኢትዮጵ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ከሲቪክ ማህበራት ጋር ጥምረት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን ገልፀው የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የመከታተልና በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችና ቅሬታዎች በህግ አግባብ እንዲፈቱ ለማስቻል እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ማቶ ማሩ በበኩላቸው ፤የሀገሪቱ ሕገ መንግስት ከሰብዓዊ መብቶች አኳያ የተዋጣለትና ዘመናዊ ሆኖ ቢቀረፅም አተገባበር ላይ ሰፊ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል።

በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው የዜጎች ሰብዓዊና መብት ጥሰት የከፋ መሆኑን አውስተው  በወቅቱ የነበሩ ሲቪክ ማህበራት ሚና ዝቅተኛ መሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው ጠቅሰዋል።

ይህም ሁኔታ ከፍተኛ ለሆነ ህዝባዊ እንቢተኝነትና ለሀገራዊ ለውጡ መነሻ መሆኑን አስታውሰዋል።

ከለውጡ በኋላ እንደ ሀገር ከተከናወኑ  የሪፎርም ሥራዎች መካከል የሲቪክ ማህበራትን ማጠናከርና አቅም ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል አሳሪ የነበሩ የሕግ ክፍተቶችን ማሻሻል ተጠቃሽ እንደሆነ አስረድተዋል።

የዘንድሮውን ምርጫ ካለፉት በተለየ ታሪካዊ የዴሞክራሲ ሽግግር የሚኖርበት ማድረግ እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ማቶ ፤ በዚህ ረገድ የአንድ አካል ብቻ ሥራ ባለመሆኑ ተባብረን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ዜጎች በሀገራቸው እጣ ፈንታ ላይ የመወሰን መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ፣በተሳትፏቸውም ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገዶችን እንዲከተሉ ለማስገንዘብ በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ሀዋሳ ቅርንጫፍ አስተባባሪ ወይዘሪት ሠላማዊት ካሳዬ  እንደ ሀገር የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን አመልክተው  ይህ ችግር በዋናነት የሚመነጨው በማህበረሰቡ ውስጥ ባለ የግንዛቤ ክፍተት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች በእኩልነትና በንቃት እንዲሳተፉ ብሎም በሂደቱ የመብት ጥሰቶች እንዳይገጥማቸው ማህበሩ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

መንግስት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል የምርጫ ሂደቱን ከማመቻቸት ጀምሮ ዜጎች ያለ ሥጋት እንዲንቀሳቀሱና በእኩልነት የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ሲቪክ ማህበራት ደግሞ ማህበረሰቡ መብቱን አውቆ የነቃ ተሳትፎ እንዲደርግ የማስተማር በሂደቱም ጥሰቶች እንዳይፈፀሙበት የመከታተል ሥራ መስራት አለብን ብለዋል።

በሀዋሳ ከተማ  ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሥልጠና   30 የሚሆኑ የሲቪክ ማህበራት አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም