ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ሚያዚያ 1/2013/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ ።

ኮሎኔል መለሰ ተሰማ ደበላ ከእናታቸው ከወይዘሮ አዛለች መረጭ እና ከአባታቸው ተሰማ ደበላ በቀድሞ ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት በ1923 ዓ.ም ነበር የተወለዱት።

እድሚያቸው ለትምህርት እንደደረሰ  በተፈሪ መኮንንና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የክብር ዘበኛ የጦር አካዳሚዎች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። 

ኮሎኔል መለስ ገና በአስራዎቹ እድሜያቸው ከመደበኛ የዘመናዊ ትምህርታቸው ወደ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል አደረጃጀት ተዘዋውረዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ጥሪ ዘመቻዎች ከተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን መካካል ኮሎኔል መለስ በኮንጎና በኮርያ በመዝመት ከአጋሮቻቸው ጋር ታርክ የማይረሳው ተግባር መፈጸማቸው ይታወሳል።

ኮሎኔል መለሰ የኮርያ ዘማቾች ማህበርን በፕሬዝዳንትነት ከ10 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን ለማህበሩ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦም አበርክተዋል።

በአገልግሎት ዘመናቸው የኢትዮጵያና የኮርያ ወዳጅነት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የስራ ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ።

ለአገር ባደረጉት ተጋድሎ ከመንግስትና ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ ሽልማት እንደተበረከተላቸው የታሪክ ድርሳናቸው ያስረዳል።

ኮሎኔሉ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ስርአተ ቀብራቸውም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ነገ ከቀኑ 6 ሰዓት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት ይፈጸማል።

ኮሎኔል መለሰ ተሰማ የሶስት ወንዶችና የሶስት ሴቶች ልጆች አባት ሲሆኑ ዘጠኝ የልጅ ልጆችንም አይተዋል።

የማህበሩ የቦርድ አባላትና የስራ ሃላፊዎች በኮሎኔል ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከ60 ዓመታት በፊት በነበረው የኮሪያ የእርስ በርስ ጦርነት በመንግስታቱ ድርጅት ጥያቄ ጦራቸውን ካዘመቱ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደነበረች ይታወቃል።

በዘመቻው ኢትዮጵያ የመጀመርያውን ቃኘው ሻለቃ ጦር ሚያዝያ 6 ቀን 1943 ዓ.ም. መላኳን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በመቀጠልም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውን እና አራተኛውን ቃኘው ሻለቆች ከ1944 እስከ 1947 ዓ.ም ወደ ስፍራው መላኳም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም