ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር ተጀመረ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2013/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የአንደኛ ዙር የክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር ተጀመረ።

ውድድሩ እስከ ሚያዝያ 3/2013 ድረስ ይካሄዳል።

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዘዳንትና የቴክኒክ ኃላፊ ኢንስትራክተር ኤልያስ ኩመል እንደተናገሩት በውድድሩ በ16 ክለቦች የተሰባሰቡ 380 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ።

በነባርና በታዳጊ ወጣቶች ምድቦች ተከፍለው በሚካሄዱት ውድድሮች 115 ሴቶችና 265 ወንዶች ይካፈላሉ።

ውድድሮቹ በፓተርን፣ በኃይል ሰበራና በልዩ ኃይል ሰበራ የሚባሉ ዘርፎች እንዳሉትም ተናግረዋል።

ውድድሮቹ ከ5 እስከ 65 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል እንደሚያሳትፍ  ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

ለውድደሩ በአነስተኛ ዘርፍ አንደኛ ለሚወጡ የወርቅ ሜዳሊያና የ1 ሺህ ብር ሽልማት ይሰጣል።

በከፍተኛ ዘርፍ አንደኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያና የ3 ሺህ ብር ሽልማት ይበረከትላቸዋል ብለዋል።

በሁለቱ ዘርፎች ሁለተኛና ሶስተኛ ሊሚወጡ ተወዳዳሪዎች የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎችና እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን ኢንስትራክተር ኤልያስ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ቴኳንዶ ስፖርት በ1985 ዓ.ም መመስረቱን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም