ቀጥታ፡

የሀዋሳ ከተማን ልማትና እድገትን ለማፋጠን የተዘጋጀ መዋቅራዊ መሪ ፕላን ይፋ ተደረገ

ሀዋሳ፣ ሚያዚያ 1 /2013 (ኢዜአ) የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ልማትና እድገት ለማፋጠን ያዘጋጀው የአስር ዓመታት መዋቅራዊ መሪ ፕላን ይፋ አደረገ።

የመዋቅራዊ ፕላኑ አካል የሆነ የሀዋሳ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ግንባታም የማስጀመሪያ መረሀ ግብር ትናንት ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የአስተዳደሩ ፕላን ኢንስቲትዩት ሃላፊ አቶ አሰፋ አፋኔ እንዳስረዱት፤ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቶ ይፋ የሆነው ፕላን ከዚህ ቀደም ለሶስት ዓመታት የነበረው የተቀናጀ ፕላን ጊዜው በመጠናቀቁ ጉድለቶችን ለመሙላት ታሳቢ ያደረገ ነው።

መዋቅራዊ ፕላኑ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት መስኮች ረገድ የተደለደለ የመሬት አጠቃቀምን በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል።

የሀዋሳ ሐይቅ፣ የመንገድ ዳርቻዎችና ተራራዎች አካባቢ የተፈጥሮ ሀብት ይዘቱን ሳይለቅ በተቀናጀ መልኩ ለማልማትና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚፈጥረው እድል ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በሀዋሳ ከተማ የነበረውን 176 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ወደ 267 ስኩዌር ኪሎ ሜትር እንደሚያሳድገውም ጠቅሰዋል።

በተባበሩት መንግስታት ሀቢታት ፕሮግራም የሀዋሳ ከተማ አዲሱ መዋቅራዊ ፕላን እንዲሰራ የ48 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ያስታወቁት ደግሞ በፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሀረገወይን በቀለ ናቸው።

ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ከተሞች እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች መነሻ በማድረግ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፈሴር ጸጋዬ ቱኬ አሁን ላይ ያለው የህዝብ ቁጥርና ፍላጎትን መሰረት በማድረግ የሚነሱ የመልካም አስተዳደርና መልማት ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ ለመመለስ አዲስ መዋቅራዊ ፕላን ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

አዲሱ ፕላን የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፉን በማስፋት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መደላድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

በተለይ የተወሳሰበ አሰፋፈር በማስቀረት ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ በተቀናጀ መልኩ በመተግበር ከተማዋን ምቹና ለኑሮ ተስማሚ ማድረግ በፕላኑ ከተካተቱ ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በተለይ የሀዋሳ ከተማን በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውሰጥ በፅዳትና በተስማሚነት በምስራቅ አፍሪካ የተሻለ ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ ግብ መያዙን አስታውቀዋል።

አዲሱን ፕላን ለመስራት የተባበሩት መንግስታት ሀቢታት ፕሮግራም ላደረገው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የመዋቅራዊ ፕላኑ አካል የሆነውና በጃፓን መንግስት ትብብር በ750 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ በሚቀጥሉት 12 ወራት ተሰርቶ የሚጠናቀቅ የሀዋሳ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ግንባታም የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሂዷል።

በመረሀ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች፣ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም