የኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት መሪ እቅድ በፕላንና ልማት ኮሚሽን ድረ ገጽ ላይ ይፋ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት መሪ እቅድ በፕላንና ልማት ኮሚሽን ድረ ገጽ ላይ ይፋ ይደረጋል
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ሙሉ መረጃው ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በፕላንና ልማት ኮሚሽን ድረ ገጽ ላይ ይፋ እንደሚደረግ ተገለጸ።
ዕቅዱ ''ፍኖተ ብልጽግና'' የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ሙሉ መረጃው ለሕዝብ ይደርሳል የተባለው የልማት እቅድ 'ሶፍት ኮፒ' በቀጣይ ሳምንት በኮሚሽኑ ድረ ገጽ ይፋ ይሆናል።
በተጨማሪም በኮሚሽኑ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ማግኘት ይቻላል።
በመጽሐፍ መልክ የተሰናዳው ሰነድ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በኅትመት ሒደት ላይ ሲሆን፣ኅትመቱ ሲጠናቀቅ በተመሳሳይ ለሕዝብ እንደሚሠራጭ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ በቀደሙ ዓመታት የልማት ዕቅድ ትግበራ ክፍተቶችን እንዲሁም የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖችን ከግምት በማስገባት በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማሳለጥ ያግዛል ተብሏል።
እቅዱ ኢትየጵያን ''አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት'' የማድረግ አገራዊ የልማት ራዕይ ለማሳካት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሎ መዘጋጀቱ ተመልክቷል።
እቅዱ መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ''ፍኖተ ብልጽግና'' አገራዊ የልማት እቅድ በሚል መጽደቁ የሚታወስ ነው፡፡
እቅዱ ከዚህ ዓመት ጀምሮ እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ የትግበራ መርሃ ግብር ተይዞለታል።