አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ዋልያዎቹን ለሁለት ዓመት ለማሰልጠን ኮንትራት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ዋልያዎቹን ለሁለት ዓመት ለማሰልጠን ኮንትራት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ሀምሌ 23/2010 አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ለማሰልጠን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የሁለት ዓመት ውል ተፈራረሙ። አሰልጣኙ ዋልያዎቹን ለሁለት ዓመት ለማሰልጠን የፈረሙ ሲሆን 125 ሺህ ብር ወርሓዊ ደሞዝ፤ ጥቅማ ጥቅሞች እና የትራንስፖረት ወጪዎች ይሸፈንላችዋል ተብሏል። በስምምነቱ መሰረቱ አሰልጣኙ ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው የ2020ው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን የመገንባት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ዛሬ የውል ስምምነት ሲያደርጉ በቆይታቸው ለጊዚያዊ ውጤት ሳይሆን ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ለመፍጠር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። እንደ አሰልጣኙ ገለጻ በረጅም ጊዜ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን መመስረት እንጂ በአጭር ጊዜ ውጤት ለማምጣት አይደለም ብለዋል። ብሄራዊ ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ አሰራርን መከተል ያስፈልጋል ያሉት አሰልጣኙ በቀጣይ አቅምን ባገናዘበ መልኩ ምክትል አሰልጣኞች፣ የምግብ፣ የአካል ብቃትና ሌሎች ባለሙያዎችን እንደሚያካትቱ ገልጸዋል። በዚህ ዓመት መጨረሻ ከሴራሊዮን ጋር ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ብሄራዊ ቡድኑ በደንብ እስከሚደራጅ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን እንደሚጠቀሙና ከአንድ ሳምንት በኃላ ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም በሀዋሳ ልምምድ እንደሚጀምሩም አስታውቀዋል። በቀጣይ ግን ወጣት ተጫዋቾች ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ለመገንባት እሰራለሁ ብለዋል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው "ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን እንዲመሰረት እንፈልጋለን፤ ይህ ደግሞ በአንድ ጊዜ የሚመጣ አይደለም ስለሆነም ለአሰልጣኙ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል" ብለዋል። "ብሄራዊ ቡድኑን እ.አ.አ በ2019 በካሜሮን በሚካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አላሳለፉም ብለን ውላችንን አናፈርስም ነገር ግን ቻን ላይ ተፎካካሪና ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን እንዲኖረን እንፈልጋለን" ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። የካፍ የአሰልጣኞች ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ከመሆናቸው በፊት የየመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩ ሲሆን የመንን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ2019 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሚካሄደው 17ኛው የእስያ ዋንጫ ማሳለፋቸው ይታወሳል። አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የቀድሞው የወንጂ ስኳር እና ጉምሩክ እግር ኳስ ቡድኖች አሰልጣኝ ሆነውም ሰርተዋል።