የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያውያንን አንድነት እያጠናከረ መሆኑን በአሶሳ ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያውያንን አንድነት እያጠናከረ መሆኑን በአሶሳ ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ
አሶሳ፤ ሚያዚያ 1/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴው ግደብ ግንባታው ሲጠናቀቅ ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የኢትዮጵያውያንን አንድነት እያጠናከረ መሆኑን በአሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ከነዋሪዎች መካከል አቶ ፈቃዱ ወዬሳ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከፍጻሜ መድረስ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው፡፡
ባለፉት አስር ዓመታትም ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ አቋም ከያዙባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ውስጥ የህዳሴው ግድብ አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የአንድታችን ምስጢር እየሆነ መጥቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አንድታችንን ያጠናከረው ግድብ በትምህርት ቤቶች ለትውልድ ማስተማሪያ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በተለይ የሃይማት አባቶች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያለልዩነት የማግኝት እድል ስላላቸው ከመንፈሳዊ ትምህርት ባሻገር የኢትዮጵያውያንን አንድነት እያጠናከረ ለሚገኘው የህዳሴው ግድብ ድጋፉን እንዲቀጥልማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አባይን ለማደናቀፍ የሚሞከረውን የውስጥ እና ውጭ ሴራ በማክሸፍ ግድቡን ከዳር ለማድረስ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ አቡዬ ሽኩር ናቸው፡፡
በየክልሉ የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በብቃት እንዲሰሩ የህዳሴው ግድብ አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሃገሪቱ ስራ አጥነትን ከመቀነስ ባሻገር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ግድቡን አስመልክቶ በውጭ የሚደረገው ጫና ግንባታውን ሲናጠናቀቅ እየቀነሰ መሄዱ እንደማይቀር አቶ አቡዬ ተናግረዋል፡፡
ሁልጊዜ በድህነት እየማቀቅን አንኖርም ያሉት አስተያየት ሰጪው የህዳሴው ግድብ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠቱ እንደማይቀር እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና ሳጅን አሰፋ ታረቀኝ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያንንን አንድ አድርጓል ብለዋል፡፡
በተለይም ግንባታው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መከናወኑ ለአካባቢው የቅርብ ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸው ፕሮጀክቱን የትኛውም ሃይል አያደናቅፈውም ብለዋል፡፡
ግድቡን ከፍጻሜ ለማድረስ ግን ከምንም በላይ አንድነታችንን ማጠናከር የግድ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አቶ ጸጋ ካባ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ የህዳሴውን ግድብ የብዙዎቻችን ተስፋ እና ሀገራችንንም ከችግር የሚያወጣ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን ለማደናቀፍ የሚደረግ የትኛውም ጥረት አይሳካም፤ ለፍጻሜ እንደተቃረበ ሁሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ አይቀርም ብለዋል፡፡
እንደከዚህ ቀደሙ አባይን እኛ ብቻ እንጠቀማለን የሚል የጎረቤት ሃገራት አካሄድ በኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ህዝብ ዘንድ መቼም ተቀባይት እንደማያገኝ አመልክተዋል፡፡
አቶ ጸጋ ኢትዮጵያውያን በፕሮጀክቱ መገንባት እየተጠናከረ የመጣውን ሃገራዊ አንድነታችንን ማስቀጠል አለብን ብለዋል፡፡