ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ ኢትዮጵያና ኳታር ወዳጅነታቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ ኢትዮጵያና ኳታር ወዳጅነታቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጠየቁ
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 ኢትዮጵያና ኳታር ያላቸውን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከርና በአገሮቹ መካከል ያሉ አካባቢያዊ ጉዳዮችን በጋራ ለመስራት እንደሚፈልጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኳታር ኤሚር ሼክ ተሚም ቢን ሐመድ አል ታኒ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አማካይነት መልእክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ በመልእክታቸው እንዳሉት ኢትዮጵያና ኳታር በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ በማጠናከር አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት ያስፈልጋል። ባለፈው ዓመት ኤምር ሼክ ተሚም ቢን ሐመድ አል ታኒና የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሁለቱ ሀገራት የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ጉብኝቶቻቸውም ሀገራቱ ተደጋጋሚ ቀረጥን በማስቀረት፣ በአየር ትራንስፖርት፣ በኢንቨስትመንት፣ ባህልና ንግድ ተባብረው ለመስራት የሚያስችሏቸውን 11 የመግባቢያ ስምምነቶች እንዲፈራረሙ አስችለዋቸዋል፡፡ በተያዘው ዓመት በኳታር የተካሔደው የኢትዮጵያ የባሕል እና ስፖርት ፌስቲቫልም የሀገራቱን ወዳጅነት ይበልጥ ማጠናከሩን የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውሷል፡፡ በዚሁ ፌስቲቫል 3 ሺህ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉ ሲሆን ዝግጅቱ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ማህበረሰብንና ኤምባሲውን ማቀራረቡም ነው በመግለጫው የተመለከተው፡፡