ቀጥታ፡

የሃይማኖት አባቶች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ወሰዱ

መጋቢት 30/2013 (ኢዜአ) የሃይማኖት አባቶች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ወሰዱ።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ተሰጣቸው።

የሃይማኖት አባቶቹ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ወቅታዊውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመከላከል ከሚወሰዱ እርምጃዎች ጎን ለጎን የቫይረሱን መከላከያ ክትባት መውሰድ ተገቢ ነው።

ክትባቱን ከወሰዱት የሃይማኖት አባቶች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ልዩ ረዳትና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ብጹዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ /ዶክተር/ ይገኙበታል።

ሕብረተሰቡ ስለ ክትባቱ ለሚነገሩ አሉባልታዎች ጆሮውን ባለመስጠትና ክትባቱን በመከተብ የተገኘውን ዕድል ሊጠቀምበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አጋጣሚውን መጠቀምና በሽታውን ይበልጥ መከላከል ይገባል ነው ያሉት።

በተመሣሣይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት ካርዲናል ብጹዕ አቡነ ብርሃነየሱስ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ወስደዋል። 

"እኔ ተከትቤያለሁ፤ እኔ ብቻዬን መከተቤ ግን ዋጋ የለውም፤ ሌሎች አቅመ ደካሞችና ለቫይረሱ የተጋለጡ ዜጎችም ይህንን ዕድል ሊያገኙ ይገባል" ብለዋል ብፁዕነታችው። 

በኮቪድ-19 የሚያዙና ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ እየተነገረ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ጥሪ አስተላልፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም