ቀጥታ፡

በኩታ በር ከተማ በቀን አንድ ሺህ ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ ተገንብቶ ማምረት ጀመረ

ደሴ ፤መጋቢት 30/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ኩታ በር ከተማ በቀን አንድ ሺህ ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በ85 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ማምራት መጀመረ።

ፋብረካው ዛሬ በተመረቀበት ስነ-ስርዓት የተገኙት የዞኑ  ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ እንዳሉት፤ በአካባቢው የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ፋብሪካው የበኩሉን አሰተዋጽኦ ይኖረዋል።

ፋብሪካው በአቅሙ ልክ ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት እንዲገባም ዞኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አታውቀዋል።

ለኢንቨስትመንት የተሰጡ ቦታዎችን  አጥረው በሚቀመጡ ላይ እርምጃ ለመውሰድ አቅጣጫ መቀመጡን  ጠቁመዋል፡፡

''እናት'' የተሰኘው  የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ይማም አሊ በበኩላቸው፤ የፋብሪካው ግንባታ በ2009 ዓ.ም. ቢጀመርም የተለያዩ ፈተናዎችን አልፎ በመጠናቀቅ ዛሬ  ወደ ማምረት መሸጋገሩን ተናግረዋል።

ፋብሪካው ለ300  ዜጎች  የስራ እድል የመፍጠር አቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ አሁን ላይ 150 ለሚሆኑ ሰዎች  የስራ እድል መፍጠር እንደተቻለ አስረድተዋል።

ፋብሪካው በቀን 500 ኩንታል ዱቄት ማምረት መጀመሩን ጠቅሰው፤ በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲገባም በቀን ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ የማምረት አቅም እንዳለው አስታውቀዋል።

የፋብሪካም ምርት ከአካባቢው አልፎ ለምስራቅ አማራ ለማዳረስ ብሎም ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እቅድ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ፋብሪካው ተጠናቆ ስራ እንዲጀምር መንግስት  ላደረገው ድጋፍ  ስራ አስኪያጁ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በፋብሪካው የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት ሰይድ አባተ በሰጠው አስተያየት ትምህርቱን ቢያጠናቅቅም ስራ በማጣቱ የቤተሰብ ጠባቂ ሆኖ እንደነበር ተናግሯል፡፡

አሁን በፋብሪካው ተቀጥሮ ስራ በመጀመሩ ራሱ ችሎ ኑሮውን ለማሻሻል እንደሚጥር ገልጿል።

በምርቃን ስነ ስርዓቱ የዞንና የወረዳ አመራሮች፤ የሐይማት አባቶችና ሽማግሌዎች ተገኝተዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ዘንድሮ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መውሰዳቸውን ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም