ቀጥታ፡

ቢጫ ቦሎቄ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለግብይት ቀረበ

መጋቢት 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቢጫ ቦሎቄ ለግብይት መቅረቡን አስታወቀ።

በዓለም ገበያ ላይ ተፈላጊነት ካላቸው ምርቶች አንዱ የሆነውን ቢጫ ቦሎቄ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቡሌ ሆራ ቅርንጫፍ አንድ ሺህ ኩንታል ምርት ባለፈው ሳምንት ተቀብሎ ለግብይት ዝግጁ ማድረጉን ምርት ገበያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ቢጫ ቦሎቄ የግብይት ክፍለ ጊዜ ወጥቶለት ለግብይት የሚቀርብ በመሆኑ ላኪዎች ምርቱን እንዲገዙ ጥሪውን አቅርቧል።

በመጪዎቹ ቀናትም ምርት ገበያው ከአርሶ አደሮች የሚቀበለውን የቢጫ ቦሎቄ ምርት መጠን እንደሚጨምርና ላኪዎች ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ላኪዎቹ ከአርሶ አደሮቹ የገዙትን የቢጫ ቦሎቄ ምርት ወደ ውጭ አገሮች እንደሚልኩም አመልክቷል።

ምርት ገበያው ከቢጫ ቦሎቄ በተጨማሪ ነጭ የእርግብ አተርና ዥንጉርጉር ቦሎቄ በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ለግብይት ያቀረባቸው ሌሎች ምርቶች መሆናቸውን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚያገበያያቸው ምርቶች ብዛት 12 ሲሆኑ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ማሾ፣ ኑግ፣ ነጭ ቦሎቄ፣ አኩሪ አተርና ፒንቶ ቢን ከሚያገበያያቸው ምርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም