የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ አስፈጻሚዎች አገራዊ ኃላፊነታቸው በአግባቡ እንዲወጡ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ አስፈጻሚዎች አገራዊ ኃላፊነታቸው በአግባቡ እንዲወጡ አሳሰበ
አዲስ አበባ መጋቢት 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ አስፈጻሚዎች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአገራዊ የኃላፊነት ስሜት እንዲወጡ አሳሰበ።
ለስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ 200 ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና ተከታትለው ወደ ሥራ መግባታቸው ይታወቃል።
ሆኖም ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከተሰማሩ አስፈጻሚዎች መካከል የተወሰኑት ''ክፍያው ያንሰናል'' በሚል ምክንያት በሥራ ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙ ቦርዱ ገልጿል።
ኢዜአ በአዲስ አበባ ከተማ ቅኝት ባደረገባቸው ምርጫ ጣቢዎች ላይ ያገኛቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች ከክፍያ ጋር በተያያዘ ቅሬታ እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ስልጠና ተሰጥቷቸው በከተማዋ የምርጫ ጣቢያዎች ከተሰማሩ አስፈጻሚዎች መካከል የተወሰኑት ሥራ ባለመጀመራቸው የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች አገልግሎት ሳይሰጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ቦርዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሌሎች የምርጫ አስፈጻሚዎችን በመመልመል አገልግሎቱ በፍጥነት እንዲጀመር ማድረጉንም ገልጸዋል።
ያልሰለጠኑ የምርጫ አስፈጻሚዎች ወደ ስለማይሰማሩ እንደአዲስ ስልጠና በመስጠት የሰው ሃይል ማሰማራትም ፈተና እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ይህም ቢሆን ግን የሰው ሃይል እጥረት ያለባቸው ቦታዎችን አዲስ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በማሰልጠን የሰው ሃይሉ እንዲሟላ መደረጉን ተናግረዋል።
ለምርጫ አስፈጻሚዎች የሚመደበው ክፍያ ለምርጫው ከተያዘው በጀት ከፍተኛ መጠን እንደሚይዝ የገለጹት ወይዘሪት ሶልያና፤ ከአገሪቱ የመክፈል አቅም አኳያ ክፍያው አነስተኛ አለመሆኑን አስረድተዋል።
"በመሆኑም የምርጫ አስፈጻሚዎች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአገራዊ የኃላፊነት መንፈስ ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።
አስፈጻሚዎቹ ኃላፊነታቸውን በትክክል በመወጣት ለኢትዮጵያ መጻኢ እድል ሚናቸውን እንዲወጡምጠይቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ክልል ውጭ በመላው አገሪቱ የመራጮች ምዝገባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።