ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስድስት ደረጃዎችን አሻሻለ

መጋቢት 30/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን /ዋልያዎቹ / በፊፋ ወርሃዊ የደረጃ ሰንጠረዠ ስድስት ደረጃዎችን አሻሻለ።

ብሔራዊ ቡድኑ በየወሩ በሚወጣው የዓለም አገራት የእግር ኳስ የደረጃ ሰንጠረዥ ባለፈው ወር 146ኛ ነበር።


በዚህ ወር በወጣው የደረጃ ሰንጠረዥ ደግሞ ስድስት ደረጃዎችን በማሻሻል 140ኛ ላይ ተቀምጧል።

ዋልያዎቹ በተያዘው ወር ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ማደጋስካርን አራት ለባዶ አሸንፈዋል። ከኮት ዲቯር ጋር በነበራቸው ጨዋታ ደግሞ ሶስት ለአንድ መሸነፋቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በምድብ 11 ተደልድላ ባጠራቀመችው ዘጠኝ ነጥብ ካሜሩን በሚቀጥለው ዓመት ለምታስተናግደው አህጉራዊ ውድድር አልፋለች።

በወርሃዊው የፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይና ብራዚል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል።

ከአፍሪካ ደግሞ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያና ናይጄሪያ በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ላይ ተቀምጠዋል።

ጅቡቲ፣ ቻድ፣ ሞሪሺየስና ደቡብ ሱዳን ደግሞ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የተቀመጡ አገራት ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም