ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በቅርቡ በጣለው ከባድ ዝናብ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ድጋፍ ተደረገ

ጋምቤላ ፤ መጋቢት 30/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በቅርቡ ነፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ ጉዳት ለደረሰባቸው ከሁለት ሺህ 400 በላይ ቤተሰቦች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስተና ኤንጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳሬክተር አቶ ጋድቤል ሙን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ድጋፉ የተደረገው በቅርቡ በጋምቤላ፣ አበቦና ኢታንግ ልዩ ወረዳዎች በጣለው ከባድ ዝናብ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ነው።

ከድጋፉ መካከል አንድ ሺህ 344 ኩንታል በቆሎ፣ ከ270 በላይ የመጠለያ ድንኳኖችና የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ይገኙበተል ብለዋል።

የምግብ ድጋፉ ለሶስት ወራት ቀለብ የሚሆን ነው።

በአደጋው ከጥቅም ውጪ ለሆኑ ትምህርት ቤቶች ተጠግነው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩም የቤት ክዳን ቆርቆሮ መመቻቸቱን ጠቅሰዋል።

የፈረሱ ከ280 በላይ መኖሪያ ቤቶች ለመጠገንም በወረዳዎች ግብር ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ጋድቤል ገልጸዋል።

ከተጎጂዎች መካከል የአበቦ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አጁሉ አጃክ በሰጡት አስተያየት በወቅቱ ጣለው ከበድ ዝናብ ቤት ንብረታቸው መውደሙን ተናግረዋል።

መንግስት የደረሰባቸውን ችግር ታሳቢ በማድረግ የምግብ እህልና የመጠለያ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው በቀጣይም የቤት መስሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መፈለጋቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ላደረጋለቸው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ በቀጣይ የቆርቆሮና የሚስማር ድጋፍ እንዲደረገላቸው የጠየቁት ደግሞ የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ኦጎቶ ኡሞድ ናቸው።

የአበቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡሞድ ኡቻላ በበኩላቸው፤ በቅርቡ በጣለው ከበድ ዝናብ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች በክልሉ መንግስትና ወረዳው  የምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስ ድጋፍ እየቀረበላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ቤታቸው ሙሉ ለሙሉ የፈረሰባቸውን ቤተሰቦች ቤት መልሶ ለመስራትም ከወረዳው አመራሮች፣ ሰራተኞችና ነዋሪዎች የቆርቆሮ፣ የእንጨትና የሚስማር ድጋፍ እየተሰባሰበ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም መንጌሽ አጎራባች ወረዳ ለተጎጂዎች ከ800 በላይ የቤት መስራ እንጨትና ሌሎች ድጋፎች መለገሳቸውንም ጠቁመዋል።

በክልሉ ሶስት ወረዳዎች በቅርቡ ንፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም