ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ነጻ የአየር ሠዓት እና የጋዜጣ አምድ ድልድል ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29/2013 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ነጻ የአየር ሰዓት እና የጋዜጣ አምድ ድልድል ይፋ አደረገ።

ቦርዱ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር በመተባበር ዛሬ የምርጫ ቅስቀሳ ነጻ የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድሉን ይፋ አድርጓል።

በዚሁ መሰረት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች ከነገ መጋቢት 30 ቀን 2013 ጀምሮ እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ድረስ በመገናኛ ብዙሃን ቅስቀሳ ማድረግ ይችላሉ፡፡

በዚህም 46 ፓርቲዎች በ21 የራዲዮ ጣቢያዎች፣ በ23 የቴሌቪዥን እንዲሁም በስምንት ጋዜጦች ተደልድለዋል ተብሏል።

ለ46ቱ ፓርቲዎች እንደ ኮታቸው 62 ሺህ 730 ደቂቃ በቴሌቪዥንና በራዲዮ እንዲሁም 615 የጋዜጣ አምድ መደልደሉም ተገልጿል።

ድልድሉ 25 በመቶ እኩል፣ ፓርቲው በሚያቀርበው የዕጩ ተወዳዳሪ ብዛት 40 በመቶ፣ እንዲሁም ፓርቲው በሚያቀርባቸው ሴት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ብዛት 20 በመቶ ነው።

እንዲሁም ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው የአካል ጉዳተኞች 10 በመቶ እና በስራ ላይ ባለው የፌዴራልና የክልል ምክር ቤት በያዙት መቀመጫ 5 በመቶውን ድርሻ የሚይዙ መሆናቸው ተመላክቷል።

የብልጽግና ፓርቲን በመወከል በመድረኩ የተገኙት አቶ ዛዲግ አብርሃ ለኢዜአ እንዳሉት ካለፉት ምርጫዎች አንጻር ለምርጫ ቅስቀሳ ብዙ ሠዓት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ድልድሉ ሕዝቡ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያካሂድ ፓርቲዎችም ራሳቸውን ለማስተዋወቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለዚህ ምርጫ ዋጋ ከፍለዋል ያሉት አቶ ዛዲግ ዕድሜው ለመራጭነት የደረሰ ኢትዮጵያዊ እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ ተወካይ አቶ ጣሂር መሀመድ በበኩላቸው በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸው የተሰጠንን የአየር ሠዓት በአግባቡ ተጠቅመን ሀሳባችንን ተደራሽ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል።

ሂደቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያበረታታ ሆኖ እንዳገኙትም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ተወካይ ወይዘሪት ትእግስት ወርቅነህም ድልድሉ በተስማማንባቸው መስፈርቶች የወጣ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሁሉንም ፓርቲ በእኩል የተመለከተና ፍትሀዊ ድልድል መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው ድልድሉ የተለያዩ መስፈርቶችን ያካተተና ፓርቲዎችም በፍትሃዊነት ድምጻቸውን የሚያሰሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

በባለስልጣኑ የተመዘገቡና እውቅና የተሰጣቸው መገናኛ ብዙሃን ብቻ እንደሚሳተፉ ገልጸው ፓርቲዎች የአየር ሠዓታቸውን በአግባቡና በጥንቃቄ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በወኪሎቻቸው በኩል የተሰጣቸውን የአየር ሠዓት ድልድል ዝርዝር ተረክበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም