በኖርዲክ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት የሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በመጪው ቅዳሜ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በኖርዲክ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት የሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በመጪው ቅዳሜ ይካሄዳል
መጋቢት 29/2013 (ኢዜአ) በኖርዲክ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የበይነ መረብ መድረክ ሚያዚያ 2 ቀን 2013 ይካሄዳል።
መድረኩ በኖርዌይ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ በኖርዲክ አገራት ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
የኢትዮጵያ ምሁራን በኖርዲክ አገራት ቡድን አስተባባሪ ዶክተር ተፈሪ ደጀኔ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በበይነ መረብ መድረኩ ከሚሳተፉ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንደሚሰባሰብና ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ዜጎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።
በውይይቱ የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃና የሶስትዮሽ ድርድሩን አስመልክቶ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በግድቡ ግንባታና ድርድር ዙሪያ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለዋል።
የበይነ መረብ ውይይቱ በሌሎች የአውሮፓ አገራት የሚኖሩ ዜጎች በተመሳሳይ ለሕዳሴ ግድቡ የሀብት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እንዲያዘጋጁ መነቃቃት የመፍጠር ዓላማ እንዳለው ነው ዶክተር ተፈሪ ያስረዱት።
የኢትዮጵያ ምሁራን በኖርዲክ አገራት ቡድን በኖርዌይ የሚገኙ የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች፣ የማኅበረሰብ መሪዎችና በአጠቃላይ በኖርዌይ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላትን ያካተተ የሕዳሴ ግድብ የሀብት አሳባሳቢ ኮሚቴ በማቋቋም ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ቡድኑ እስካሁን ለሕዳሴ ግድብ 1 ሚሊዮን ብር ማሰባሰቡንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የምሁራኑ ቡድን በኖርዲክ አገራት ለሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናትና ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎችና ሃላፊዎች በሕዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያ አቋም ዙሪያ መረጃ በመስጠት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከተቋቋመ አንድ ዓመት ገደማ የሆነው የምሁራን ቡድን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ እየሰራ እንደሆነ ነው ዶክተር ተፈሪ ያስረዱት።
በኖርዲክ አገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር ድሪባ ኩማ በበኩላቸው በኖርዲክ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በገንዘብና በእውቀት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
በስዊድን ስቶክሆልም የሚገኘው ኤምባሲ ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ እስካሁን በኖርዲክ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ /300 ሺህ የስዊድን ክሮነር/ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
ኤምባሲው በአጠቃላይ በ2013 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከኖርዲክ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ /400 ሺህ የስዊድን ክሮነር/ ለመሰብሰብ ማቀዱንም ጠቁመዋል።
በኖርዲክ አገራት የሚገኙ ዜጎች ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በሚኖሩባቸው አገራት ባቋቋሟቸው ቡድኖችና ማኅበራት የሕዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የማስረዳት ስራ እየከወኑ ነው ብለዋል።
በተለይም ግድቡን አስመልክቶ የሚሰራጩ የተዛቡና አሳሳች መረጃዎችን በማጋለጥ አገራትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሚዛናዊ ምልከታ እንዲኖራቸው እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ኤምባሲው የሕዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ወቅታዊ መረጃዎችን ለኢትዮጵያዊያኑ እየሰጠ እንደሚገኝም ነው አምባሳደር ድሪባ ያስረዱት።
ኤምባሲው በሚሸፍናቸው የኖርዲክ አገራት ማለትም ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ዴንማርክና ፊንላንድ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን የማልማት መብቷን እንደሚገነዘቡና በሶስትዮሽ ድርድሩ የሚነሱ ጉዳዮችን በውይይት መፍታት እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውንም ነው የጠቆሙት።
በኖርዲክ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከሕዳሴው ግድብ በተጨማሪ ለገበታ ለአገር፣ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝና ለአንበጣ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም ለሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም አክለዋል።
በመጪው ቅዳሜ በሚካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀብት ማሰባሰቢያ የበይነ መረብ ምክክር መድረክ ከ300 በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።