የህዳሴ ግድብ ድርድር ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርጉ ሃሳቦች ላይ ተመስርቶ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ፅኑ አቋም አላት - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ድርድር ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርጉ ሃሳቦች ላይ ተመስርቶ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ፅኑ አቋም አላት
አዲስ አበባ፣ መጋቢት29/2013 (ኢዜአ) የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩ በትብብርና ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርጉ ሃሳቦች ላይ ተመስርቶ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፅኑ አቋም መሆኑን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሶስቱ አገራት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ያደረጉትን የሶስትዮሽ ድርድር በማስመልከት ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኪንሻሳው ድርድር በተለይ ኮቪድ 19 በአለም ላይ ከተከሰተ በኋላ ሶስቱን አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ፊት ለፊት ያገናኘ ነበር።
በአፍሪካ ህብረት በኩል በተጠራው ስብሰባ የሶስቱም አገራት የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የቴክኒክ ባለሙያዎችና የታዛቢዎች ቡድንም ታድመዋል።
በውይይቱ መክፈቻ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባደረጉት ንግግር ኢትዮጰያ ድርድሩ ቀጥሎ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ፅኑ ፍላጎት እንዳላት ማብራራታቸውን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ሰንቆ ለቀጣናው ትልቅ የልማት ትብብር የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
''ኢትዮጵያ በግድቡ ማንንም በጉልህ የመጉዳት እንዲሁም የብቸኛ ተጠቃሚነት አስተሳሰብ የላትም'' በማለት ድርድሩ በትብብርና ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርጉ ሃሳቦች ላይ ተመስርቶ መከናወን እንዳለበት አፅኖት መስጠታቸውን ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ገልጸዋል።
ግድቡ በተለይም ከፍተኛ የውሃ መጠን በሚገኝበት የክረምት ወቅት ደረጃ በደረጃ የሚሞላ በመሆኑ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት አያደርስም ነው ያሉት።
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ በተለይ ሱዳን በግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ምክንያት የውሃ እጥረት እንደገጠማት አድርጋ ማቅረቧ ከእውነታ የራቀ መሆኑን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ገልጸዋል።
በግድቡ ምክንያት ኢትዮጵያ በሱዳንም ይሁን በግብፅ ህዝብ ላይ ጉልህ ጉዳት የማድረስ አላማ እንደሌላት አረጋግጠዋል።
ግብጽና ሱዳን ቀደም ሲል መስማማት ላይ የተደረሰባቸው ነጥቦችን እንደ አዲስ በማንሳት ድርድሩ እንዲዘገይ እያደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የግድቡን ውሃ ሙሌት ማስተጓጉል ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ኪሳራ ከመሆኑ ባለፈ በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለው ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
የግድቡ ግንባታ በዘገየ ቁጥር ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቀጥታ የምታገኘውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ታጣለች ብለዋል።
በህዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ደርድር አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረትና ደቡብ አፍሪካ በታዛቢነት እየተሳተፉ መሆኑ ይታወቃል።
ይሁንና በኪንሻሳው ድርድር ግብጽና ሱዳን ከመርሆ ስምምነት ውጭ የአፍሪካ ህብረትን ሚና በማሳነስ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ እንዲገባ ያሳዩትን ፍላጎት በኢትዮጵያ በኩል ውድቅ ተደርጓል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ትልቅ መተማመን እንዳላትና ድርድሩም በህብረቱ አመቻችነት መቀጠል እንዳለበት ፅኑ አቋም አላት ሲሉ ዶክተር ስለሺ ገልጸዋል።
የሶስትዮሽ ደርድሩ በመጪው ሚያዝያ 20 እንዲቀጥል ሀሳብ የነበረ ቢሆንም በግብጽና ሱዳን ተለዋዋጭ አቋም ምክንያት እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።
የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር በሚሰጡት ውሳኔ መሰረት ኢትዮጵያ ድርድሩን ለመቀጠል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።