ቀጥታ፡

በመዲናዋ የአገልግሎት ፈላጊዎች ጥግግት ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት አጋላጭ ነው

መጋቢት 29/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የማስክ አጠቃቀም ቢሻሻልም በአገልግሎት መስጫ አካባቢዎች የእርስ በእርስ ጥግግቱ ለቫይረሱ ስርጭት አጋላጭ እንደሆነ ይስተዋላል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ዜጎችን ለማኅበራዊ ቀውስ እየዳረገ ነው።

የሟቾችና ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ገብተው የሰውና የመሳሪያ እርዳታ የሚሹ ታማሚዎች ቁጥር መጨመርም ከአቅም በላይ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል።

በመሆኑም መንግስት የቫይረሱን ስጭት ለመከላከል ወጥቶ የነበረውን አስገዳጅ መመሪያ ማስተግበር መጀመሩ ይታወቃል።

ይህን መመሪያ የጣሰ ግለሰብ ከ10 ቀን እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት እንደሚጣልበት ተደንግጓል።

ከመመሪያው ትግበራዎች አንዱ ማስክ ማድረግና ርቀትን የመጠበቅ ግዴታዎች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአዲስ አበባ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የትራንስፖርት መጠቀሚያዎችን ቃኝቷል፤ የአገልግሎት ፈላጊዎች ጥግግት መመሪያውን የጣሰ እንደሆነም ታዝቧል።

የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሃላፊዎች እንደሚሉት መመሪያውን ለማስተግበር ተገልጋዮችን ሰልፍ በማስያዝና ውስን ሰዎችን በየተራ በማስገባት አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ እየሰሩ ነው።

ይሁንና አብዛኛው ተገልጋይ ርቀቱን ጠብቆ እንዲስተናገድ ቢነገረውም ለቫይረሱ ቸልተኛ ሆኗል ነው የሚሉት።

በዚህ ሳቢያ የተቋማት ሠራተኞች ለቫይረሱ ተጋላጭ እየሆኑ ስራም እየተበደለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኀብረተሰቡ የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያዎችን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ እንዲፈፅም አሰራር ቢዘረጋም የሚጠቀመው ሰው ቁጥር አናሳ ነውም ብለዋል።

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ የቅርንጫፍ 5 ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ደባሱ እና የሰሜን አዲስ አበባ ዲስትሪክት ቁጥር 1 ደንበኞች አገልግሎት ሃላፊ አቶ ይገረም ጥላሁን ይህንኑ ነው የገለጹት።

አስተያየታቸውን የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ደግሞ መዘናጋቱ ከመንግስትና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይጀምራል ነው የሚሉት።

ለዚህም ቫይረሱ እንደተከሰተ በየተቋማቱ ደጃፍና በመንገዶች ላይ የንጽህና መጠበቂያዎች ተቀምጠው ኅብረተሰቡም ይጠቀምባቸው እንደነበረ አሁን ይህ እንደተረሳ ይገልጻሉ።

የመንግስት ሃላፊዎችም በየመድረኩ አስገዳጅ ሕጎችን ሲጥሱ ኅብረተሰቡ ሲመለከት የቫይረሱ ስርጭት እንደሌለ በማሰብ ችግሩን አባብሶታል ይላሉ።

በእነዚህና በሌሎች የተሳሳቱ አመለካከቶች ምክንያት መዘናጋቱ መባባሱን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወሉ ሱልጣን የወጣውን መመሪያ በመተግበር ተቋማትና የመንግስት ባለስልጣናት ቀዳሚውን ስፍራ በመያዝ ዓርአያ መሆን አለባቸው ይላሉ።

አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ክልከላው እንዲተገበርና የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ አበክረው መስራት አለባቸው ብለዋል።

ይህን ለማስተግበር የተቋቋመው ኮሚቴ መመሪያውን በማይተገብሩ ተቋማት ጥቆማ ከደረሰው እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቀዋል።

በቅርቡ መተግበር የጀመረው አስገዳጅ ሕግ ለውጥ እያመጣ ቢሆንም ሌሎች ሃሳቦችን የሚያነሱ አሉ ብለዋል አቶ አወሉ።

የመመሪያው ዓላማ ሰዎችን መቅጣት ሳይሆን መመሪያዎችን በማስተግበር ዜጎችን ከሚደርስባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መታደግ እንደሆነም ይጠቅሳሉ።

ይሁንና አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች መንግስት የምርጫ ቅስቀሳን ለመገደብ አስቦ ያደረገው ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳላቸው መረዳት ተችሏልም ብለዋል።

ነገር ግን ይላሉ ሃላፊው መመሪያው የወጣው ዜጎችን ከቫይረሱ ስርጭት ለመታደግ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመመሪያው መሰረት ለሚመለከተው ክፍል አሳውቀው የምርጫ ቅስቀሳና ስብሰባቸውን ማካሄድ ይችላሉ ብለዋል።

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የወጣውን መመሪያ በማክበር የምርጫ ቅስቀሳቸውን ማድረግ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የሚጠቀሙ ዜጎች ቁጥር መጨመሩንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም