ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ከግራንት ቶረንተን ኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

መጋቢት 29/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ግራንት ቶረንተን ኢትዮጵያ ከተባለ አለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ጋር የቁጥጥር አቅም ግንባታን ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱ የባለስልጣኑን የቁጥጥር አቅም ግንባታን ለማጠናከር የሚያስችል ፕሮጀክት ሰነድ ለማዘጋጀት እና ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኡሌሮ ኡፒዮው እንደገለጹት፤  በአገሪቱ ዘመናዊ፣ ውጤታማ፣ ግልጽ እና የተረጋጋ  የግብይት ስርአት መገንባት ያስፈልጋል።

ለዚህም የቁጥጥር እና የድጋፍ ተግባራትን በማጠናከር የሻጮች፣ የገዢዎችን እና አጠቃላይ የህብረተሰቡን ጥቅም ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በስምምነቱ በተለይ በቁጥጥር አቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ፣ በአቅም ግንባታ ስልጠና፣ ወጪና ጊዜን የሚመጥን አደረጃጀት በመዘርጋት እና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ያስችላል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ስራ ላይ ሲውልም የቴክኖሎጂ እና የተቋሙን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የግብይት ስርአት እንዲኖር ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ነውም ብለዋል።

የግራንት ቶረንተን ኢትዮጵያ አማካሪ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ኤሚያስ እሸቱ፤ ፕሮጀክቱ የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ረገድ ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል።

የአቅም ክፍተትን በጋራ በመለየት እና ሃብት በማፈላለግም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የፕሮጀክት ሰነዱ አጠቃላይ ዝግጅት እና የትግበራ ሂደት ለሚቀጥሉት ሶስት አመታት የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል።

የግራንት ቶረንተን ለመንግስታዊና የግል ሴክተሮች እንዲሁም አነስተኛና መካከለኛ የግል ተቋማት ዓለም አቀፍ ተሞክሮን፤ የቢዝነስና የልዩ ክህሎት እውቀቶችን የሚያጋራ ተቋም መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም