ቀጥታ፡

መጪው ምርጫ የሕዝብ ድምጽ ዋጋ የሚያገኝበት እንዲሆን ኃላፊነታችንን እንወጣላን - የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች

መጋቢት 29/2013 (ኢዜአ) በመጪው ምርጫ የሕዝብ ድምጽ ካለፉት ምርጫዎች የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።

አገራዊውን ምርጫ ለመታዘብ 155 ገደማ አገር በቀል የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ወስደዋል።

ከእነዚህ መካከል የሆነው የኢትዮጵያ ወጣቶች ሠላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ለመራጮች ትምህርት ለመስጠትና ምርጫውን ለመታዘብ ፈቃድ አግኝቶ በዝግጅት ላይ መሆኑን የሊጉ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ በቀለ ይገልጻሉ።

እስካሁንም በአዲስ አበባ ለወጣቶች፣ ለሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች ከምርጫ ጋር የተያያዘ ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።

በዚህም ከመዲናዋ ሁሉም ክፍለከተሞች የተወጣጡ 1 ሺህ 500 ወጣቶችና ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች መካተታቸውን ጠቅሰዋል።

የምርጫውን ሂደት ፍትሃዊነት ለመታዘብ 101 ወጣቶችን በመላ አገሪቷ ለማሰማራት መታቀዱንም ነው የገለጹት።

የምርጫውን ሂደት ለመታዘብ ፈቃድ ያገኘው ሌላው አገር በቀል ድርጅት 'ፕሮ ዴቨሎፕመንት ኔትወርክ' ይሰኛል።

የዚህ ድርጅት ኃላፊና የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ሁሴን ለምርጫው ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አህመድ መጪው ምርጫ በአይነቱ ልዩና መሸጋገሪያም እንደሚሆን በብዙዎች ዘንድ ተስፋ አሳድሯል ይላሉ።

ምርጫው ፍትሃዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ለውጤት እንዲበቃ ሂደቱን በቀናነት መታዘብ ይገባል ነው ያሉት።

ይህን ለማሳካት የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ጥረት እንዳለ ሆኖ፤ የሁሉም ድርሻ ትልቅ በመሆኑ የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

ከትግራይ፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝና ከጋምቤላ ክልሎች ውጭ በመላ አገሪቷ ከ200 እስከ 300 በሚደርሱ ወጣቶች ምርጫውን ለመታዘብ ያቀደው ደግሞ 'ቼንጅ ፎር ኢትዮጵያ' የተባለው ድርጅት ነው።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፉአድ ጀማል እንደሚሉት ለታዛቢነት የተዘጋጁት ግለሰቦች ምርጫውን ነጻ ሆነው እንዲመለከቱ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው።

"ምርጫ ነገ ትልቅ ነገር ይዞ የሚመጣ ነው፤ ምክንያቱም ነገ መንግሥት የምናስቀምጥበት በመሆኑ ከየትኛውም ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ መታዘብ ይገባል" ብለዋል።

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በመጪው ግንቦት መጨረሻና ሰኔ መጀመሪያ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም