ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዛሬ ማምሻውን በድሬዳዋ ቀጥሎ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዛሬ ማምሻውን በድሬዳዋ ቀጥሎ ይካሄዳል
መጋቢት 29/2013(ኢዜአ) አራተኛው ዙር የቤትኪንግ የወንዶች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ውድድር ዛሬ ማምሻውን በድሬዳዋ ይጀመራል።
ለውድድሩ የልዑካን ቡድን አባላት ትናንት የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በተገኙበት የእራት ግብዣ ተደርጎላቸዋል፡፡
ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ውድድሩ በስኬት እስኪጠናቀቅ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡
ከስፖርት በዘለል ይህ ውድድር ድሬዳዋ ለኢንቨስትመንትም ሆነ ለንግድ ሥራ ትክክለኛ ስፍራ መሆኗን ለማሳወቅም መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አስታውቀዋል፡፡
ውድድሩ የድሬዳዋ ሁለንተናዊ የስፖርት እንቅስቃሴዎችንና ተተኪዎችን ለማፍራት የተጀመረውን ጥረት ለማነቃቃት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ ናቸው፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድና የካቢኔ አባላት ውድድሩ የሚኪያሄድበት የድሬዳዋ ስታዲዮም በመገኘት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም ተመልክተዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሰለሺ ሰለሞን በፕሮጀክት የታቀፉ ተተኪዎች የሚወዷቸውን የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በልምምድ ቦታ ተገኝተው መመልከታቸው ለነሱ ጥሩ ተነሳሽነትይፈጥራል ብለዋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለቦችን እያስተናገደ የሚገኘው የሣምራት ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ተሾመ ውድድሩ የፍቅር ከተማ በሆነችው ድሬዳዋ መካሄዱ የርስበርስ ግንኙነትና አንድነትን ለማጠናክር ያግዛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንግዶቹ በቆይታቸው የሚያስደስትና የሚያረካ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዛሬ ማምሻውን ሲጀመር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰበታ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና ከሃዋሳ ከተማ እንደሚጋጠሙ ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል፡፡