ኢንጂነር ስመኘውን በሞት ብናጣም ለግድቡ ድጋፍ በማድረግ የጀመሩትን ከግብ እናደርሳለን...የዲላ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢንጂነር ስመኘውን በሞት ብናጣም ለግድቡ ድጋፍ በማድረግ የጀመሩትን ከግብ እናደርሳለን...የዲላ ከተማ ነዋሪዎች

ዲላ/ደብረብርሃን ሀምሌ 23/2010 የልማት አርበኛው ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በሞት ቢለዩም ለግድቡ ግንባታ ድጋፋቸውን በማጠናከር የጀመሩትን ሥራ ከግብ እንደሚያደርሱ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። የደብረ ብሃን ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ በነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል። በኢንጂነሩ ሞት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው የገለጹት ነዋሪዎቹ በኢትዮጵያ ህዝብ አሻራ እየተገነባ ያለው የህዳሴው ግድብ ለአፍታም እንዳይቋረጥ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ለአዜአ ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ዳንኤል ከተማ እንዳሉት የግድቡን ሥራ በግንባር ቀደምነት ሲመሩ የነበሩት ኢንጂነር ስመኛው ዛሬ በህይወት ባይኖሩም የግድቡ ሥራ ለአፍታም አይቋረጥም። ለእዚህም ከእዚህ በፊት በቦንድ ግዥና በተለያዩ ተግባራት ሲያካናውኑት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት፡፡ ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያዎችም ሆነ በግለሰቦች ለሚተላለፉ ተጨባጭ ያልሆኑ መልዕክቶች ጆሮ ሳይሰጥ ክስተቶችን በተረጋጋ መንፈስ በማየት ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ "የኢንጂነር ስመኘው በቀለ መሞት የቤተሰብ አባሌን በሞት ያጣሁ ያህል ነው ሀዘን እንዲሰማኝ ያደረገው" ያሉት ደግሞ አቶ ግርማ ተሰማ የተባሉ ሌላው የዲላ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ኢንጂነር ስመኘው በኢትዮጵያ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ላይ የመሪነት ሚና የተጫወቱ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለአገሪቱና ለህዝቡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሰው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ "የኢንጂነሩ አሟማት ለነገ ተብሎ የሚተው ጉዳይ አይደለም፤ በጉዳዩ እጃቸው ያሉ ግለሰቦች ካሉ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ ወስዶ ለህግ መቅረብ ይኖርበታል" ብለዋል ፡፡ ኢንጂነር ስመኘውን ሊተኩ የሚችሉ በርካታ ባለሙያዎችን አገሪቱ ማፍራቷን የጠቀሱት አቶ ግርማ " ግድቡ ለአፍታም እንዳይቋረጥ ሳደርገው የነበረውን ድጋፍ አጠናክሬ እቀጥላለሁ" ብለዋል ፡፡ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በርሀ ሳይበግራቸው ለአገሪቱ ልማት ደፋ ቅና ሲሉ የነበሩ ታላቅ ሰው እንደነበሩ የገለፁት ደግሞ አቶ ደርቤ ጅኖ የተባሉ የዲላ ከተማዋ ነዋሪ ናቸው። የኢንጂነሩ ሞት እጅግ የሚያሳዝንና ልብ የሚነካ መሆኑን የገለጹት አቶ ደርቤ፣ መንግስት የሞታቸውን መንስኤ በአፋጣኝ አጣርቶ ለህዝብ ማሳወቅ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ የልማት አርበኛው በሞት ቢለዩም ለአገር ባበረከቱት ሥራ በኢትዮጵያውያን ልብ ወስጥ ሁሌም ሲታወሱ እንደሚኖሩ ተናግረው፣ ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ ድጋፉን በማጠናከር ህልማቸውን ከግብ ማድረስ እንዳለበትና ለእዚህም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ ዜና የደብረ ብሃን ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ በነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ለኢዜአ በላከው የሀዘን መግለጫ እንዳስታወቀው ኢንጅነር ስመኘው የሕዳሴው ግድብ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በብቃት በመምራት ላከናወኑት አርያነት ያለው ተግባር ዩኒቨርሲቲው አድናቆቱን ይገልጻል። የልማት ጀግናው በደረሰባቸው ድንገተኛ ሞት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት መሪር ሀዘን እንደተሰማቸው የገለጸው መግለጫው፣ በቀጣይ ግድቡን ከፍጻሜ ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ የዩኒቨርሰቲው ማህበረሰብ አባላት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አርጋግጧል።