ቀጥታ፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ በአቡነ መርቆሪዎስ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ያሳለፈውን ቃለ ውግዘት አነሳ

አዲስ አበባ ሀምሌ 23/2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት የተላለፈውን ቃለ ውግዘት አነሳ። ሲኖዶሱ ቃለ ወግዘቱን ያሳለፈው በ1984፣ 1985 እና 1999 ዓ.ም ሲሆን፤ ሰሞኑን በአሜሪካ የተደረገውን የሰላም ስምምነት መሰረት ቃለ ውግዘቱን ማንሳቱን ገልጿል። ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ቤተክርስቲያኗ አንድነቷን ጠብቃ ለአገሪቱ ሰላምና ደህንነት ብዙ ሰርታለች። ከሁለት አስርት አመታት ወዲህ ያልተጠበቁ ችግሮች ተፈጥረው በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል መለያየት መፈጠሩን አስታውሰዋል። በተፈጠረው መለያየት የተነሳም አባቶች ከውድ አገራቸው ወጥተው በሰሜን አሜሪካ እንዲኖሩ ከማድረጉም በላይ ቃለ ውግዘት አስከትሎ እንደነበር አቡነ ዲዮስቆሮስ ገልጸዋል። በመሆኑም በአባቶች መካከል እርቀ ሰላም በመውረዱና ስምምነት ላይ በመደረሱ በቅዱስ ሲኖዶሱ በተለያየ ጊዜ የተላለፈው ቃለ ውግዘት እንዲነሳ መወሰኑን ተናግረዋል። እርቀ ሰላሙ እንዲወርድ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ አካላትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአባቶች መካከል ለተደረገው እርቀ ሰላም ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በኢትዮጵያና በአሜሪካ በሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ችግር እርቀ ሰላም በማውረድ መፈታቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም