ቀጥታ፡

አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን የቱርክ አምባሳደር ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አደረጉ

መጋቢት 28/2013 (ኢዜአ) በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን የቱርክ አምባሳደር ኢርፋን ናዚር ኦግሉን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም ሁለቱ አምባሳደሮች በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነትና የኢኮኖሚ ትስስር አድነቀው ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል ።

በተጨማሪ አምባሳደር ይበልጣል በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ ከዚህ ቀደም በተቋቋሙ የጋራ ኮሚቴዎችና የሕግ ማዕቀፎች መሰረት በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ዝግጁነት ያስረዱ ሲሆን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት ዙሪያም የኢትዮጵያ ፍትኃዊና ምክንያታዊ አቋም በተመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አክለውም መንግስት በትግራይ ክልል ለሰብዕዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና የዓለምአቀፍ ሚዲያ ተቋማት ያልተገደበ ፈቃድ መስጠቱን ጨምሮ ሌሎች ከሰብዕዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተገናኘ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዐዊ መብት ተቋማት ጋር የጋራ ምርመራ ለማድረግ ስለተጀመሩ ስራዎች ገለጻ አድርገዋል።

አምባሳደር ኢርፋን በበኩላቸው ለተደርገላቸው ገለጻ አመስግነው በቀጣይ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀራርቦ ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት ማረጋገጣቸውን በሱዳን የኢትዮጵያ ኢምባሲ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም